በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩኤሴኤይድ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የምግብ ርዳታ እንደሚቀጥል አስታወቀ


የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤሴኤይድ)፣ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የምግብ ርዳታ፣ ከአምስት ወራት መቋረጥ በኋላ በመጪው የፈረንጆች ወር እንደሚቀጥል አስታውቋል። ርዳታው ተቋርጦ የነበረው ለተረጂዎች መዳረስ የነበረበት ምግብ በአካባቢ ባለሥልጣናት እውቅና ጭምር ለገበያ ቀርቧል በሚል ነበር።

ዩኤሴኤይድ ባለፈው ወር አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑና በኢትዮጵያ ለሚገኙ ፍልሰተኞች ርዳታ መስጠቱን ቀጥሎ ነበር። ይህም መንግስት ምግብ ለፍልሰተኞች በማዳረስ ሥራ ውስጥ እንደማይገባ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ መሆኑን የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጀሲካ ጀኒንግስ ትናንት እንደገለጹት፣ ርዳታው እንዲቀጥል የተደረገው የተረጂዎችን ምዝገባ እና የታደለው እህል መድረሱን ማረጋገጥ በተመለከተ አዲስ የተሻሻለ አሠራር መዘርጋቱን ተከትሎ ነው።

አዲሱ አሰራር ለአንድ ዓመት እንደሚሞከር እና ርዳታው ምግብ ለሚያስፈልጋቸው መድረሱን በማረጋገጥ፣ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የምግብ ርዳታ አሰራር እንደሚቀይረው ቃል አቀባይዋ ጨምረው ገልጸዋል።

ዩኤሴኤይድ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለርዳታ የቀረበ ምግብ በመንግስት ባለሥልጣኖች ተሰርቋል በሚል ባለፈው መጋቢት ለትግራይ ክልል የሚሰጡትን ርዳታ አቋርጠው ነበር። ባለፈው ሰኔ ደግሞ ችግሩ በመላ አገሪቱ የሚታይ ነው በሚል፣ ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን ርዳታ ሙሉ ለሙሉ አቋርጠው ነበር።

በርዳታ እህል ስርቆት ታሪክ ከፍተኛው ምዝበራ እንደነበር ዩኤሴኤይድ አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG