በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሳማንታ ፓወር የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝት


የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩኤስኤአይዲ/ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሼኽ ሞሃሙድ
የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩኤስኤአይዲ/ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሼኽ ሞሃሙድ

በምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ /ዩኤስኤአይዲ/ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ትናንት፤ ዕሁድ ከሶማሊያ ፕሬዚደንት ሃሰን ሼኽ ሞሃሙድ ጋር ሞቃዲሾ ላይ ከተነጋገሩ በኋላ ሃገራቸው ሶማሊያን የገጠሟትን ሰብዓዊ ቀውሶች ለመዋጋት የሚያስችል ተጨማሪ ዕርዳታ እንደምትለግስ አስታውቀዋል።

ዋና አስተዳዳሪዋ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት ቃል ሶማሊያ በብዙ አካባቢዎቿ ላይ ብርቱ ጉዳት ያስከተለባትን የተራዘመ ድርቅ እንድቋቋም ለማገዝ ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ ዕርዳታ እንደምትለግስ ተናግረዋል።

በያዝነው ዓመት ውስጥ አሜሪካ ለሶማሊያ ህዝብ ሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጓን ማመልከታቸውን ኤጀንሲያቸው ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።

ሶማሊያ የምግብ ቀውስ አብዝቶ የጠናባት ሀገር መሆኗን ሳማንታ ፓወር ጠቅሰዋል።

"ይህ እንደሌላው ድርቅ አይደለም። እንደሌሎቹ አጣዳፊ ሁኔታዎች አይደለም። ለአራት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች በቂ ዝናብ አልጣለም። አሁን እያየን ያለነው በሚሊዮኖች በሚቆጠር ህዝብ ላይ እያንዣበበ ያለ ታይቶ የማያውቅ ጥፋት ነው” ብለዋል።

ሌሎች ሀገሮችና ለጋሾች እንዲሁም ግለሰቦች ለሶማሊያ የዕርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ የዩኤስኤአይዲ ዋና አስተዳዳሪ ፓወር ተማፅነዋል።

ይሁን እንጂ ዕርዳታውን ለተረጂው የማድረስን ጉዳይ በሚመለከት ዩናይትድ ስቴትስ ብርቱ ሥጋት ያላት መሆኑንና ችግሩን ለማቅለል እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኗን ሞቃዲሾ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

"ይህን የምናደርገው ለዕርዳታ የተመደበ ገንዘብ የግል ጥቅማቸውን ከተራቡ ሰዎች በሚያስቀድሙ ግለሰቦች እንዳይሰረቅ ለመከላከል መሆኑን አጥብቄ ላስገነዝብ እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ከሶማሊያ ህዝብ ግማሹ ማለትም 7 ሚሊዮን 7 መቶ ሺህ የሚሆነው ዕርዳታ ጠባቂ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ትናንት፤ ዕሁድ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ሳማንታ ፓወር ከትናንት በስተያ ቅዳሜም ኬንያ ውስጥ ለድርቅና ለረሃብ የተጋለጡ ኬንያዊያንን ያሉበት ሄደው ተመልክተዋል፤ አነጋግረዋቸዋል።

‘አካባቢው ላይ የደረሰውን ድርቅና የምግብ ቀውስ አጉልቶ ለማሳየት የታለመ ነው’ በተባለ ጉብኝታቸው ሚስ ፓወር ቱርካና ክፍለግዛት ውስጥ የካቾዳ መንደር ነዋሪዎችን ሄደው አነገግረው ድርቁ በማኅበረሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ሰፊ ጉዳትና የደቀነውን የቸነፈር ሥጋት መመልከታቸው ተዘግቧል።

"ያነጋግርኳቸው እናቶች ልጆቻቸው ምግብ በማጣት ተጎድተውባቸዋል። እንስሶቻቸው በሙሉ አልቀውባቸዋል። በመተዳደሪያቸው ላይ ብርቱ ጉዳት ደርሷል፤ ሰዎች በገፍ ለሞት የሚጋለጡበት አደጋም ተደቅኗል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“ዩናይትድ ስቴትስ ለአጋሮቿ የአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ትለግሳለች” ብለዋል ሳማንታ ፓወር።

ለአራት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ሳይጥል በቀረበት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የከፋ ሰብዓዊ አደጋ መደቀኑን የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት፥ የዕርዳታ ድርጅቶችና ሌሎችም ለበርካታ ወራት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

ባለፈው ዓርብ የምሥራቅ አፍሪካ ሃገሮች የጋራ ልማት ተቋሙ ኢጋድ ያወጣው ግምገማ በአካባቢው በዚህ የአውሮፓ ዓመት ከሃምሳ ሚሊዮን የሚበልጥ ሰው ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት እንደሚጋለጥ አሳስቧል።

በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ሦስት መቶ ሺህ ሰዎች ለረሃብ ቸነፈር እንደሚጋለጡ ኢጋድ ሥጋቱን አክሎ አሳውቋል።

XS
SM
MD
LG