በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሳዑዲው ጋዜጠኛ ጃማል ኻሾጊ ደብዛ መጥፋት እንዳሳሰባቸው ላንሲንግ አስታወቁ


ጃማል ኻሾጊ - የሳዑዲ አረቢያ ጋዜጠኛ
ጃማል ኻሾጊ - የሳዑዲ አረቢያ ጋዜጠኛ

“ማንም ቢሆን፤ በተለይ መንግሥታት የጋዜጠኞችን አንደበት እንዲዘጋ ሊፈቀድለት አይገባም” ብለዋል የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃን ላንሲንግ ዛሬ ባወጡት መግለጫ።

የሳዑዲ አረቢያ ጋዜጠኛ የሆነውና ለዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ የሚፅፈው የጃማል ኻሾጊ ደብዛ ድንገት መጥፋት በጥልቅ ያሳሰባቸው መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲ /ዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም./ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃን ላንሲንግ አስታወቁ።

ኻሾጊ የሚገኝበት ቦታና ሁኔታ እንዲታወቅ እየጎተጎቱ ካሉ የሚድያ፣ የመንግሥታትና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋማት መሪዎች የተባበረ ጥረት ጋር እንደሚቀላቀሉም ሚስተር ላንሲንግ ዛሬ በፅሁፍ ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል።

ጃን ላንሲንግ - የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲ /ዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም./ ዋና ሥራ አስፈፃሚ
ጃን ላንሲንግ - የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲ /ዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.ኤም./ ዋና ሥራ አስፈፃሚ

“ይህ አጋጣሚ፤ በሚያሳዝን ሁኔታ በፕሬስ ላይ በዓለም ዙሪያ እያደገ የመጣው ሥጋት አካል ነው” ብለዋል ላንሲንግ። “የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲ መረብ አካላት ለሆኑት ለአሜሪካ ድምፅ፣ ለነፃ አውሮፓ ራዲዮ /ራዲዮ ሊበርቲ/፣ ለኩባ ብሮድካስቲንግ ቢሮ፣ ለነፃ እስያ ራዲዮና ለመካከለኛው ምሥራቅ ብሮድካስቲንግ መረብ የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በመላው ዓለም ያሉ ጋዜጠኞች እውነትን ለመዘገብ ሲንቀሣቀሱ በየዕለቱ በሕይወታቸውና በኑሯቸው ላይ አደጋ ይደቀንባቸዋል” ብለዋል በማከል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው በመቀጠልም “በዓለም ዙሪያ ያሉ በሙስና የተዋጡና ጨቋኝ መንግሥታት መረጃን የመቆጣጠርና ነፃ ሚድያን የማፈን ባሕርይን ይጋራሉ” ብለዋል።

“ነፃ ጋዜጠኞች ሥጋት ስለሚያሳድሩባቸው የእነዚያን ጋዜጠኞች መተኪያ የሌለው ተግባር በወንጀልነት ይፈርጁታል” ሲሉ አመልክተዋል የዩ.ኤስ.ኤ.ጂ.አም. ዋና ሥራ አስፈፃሚ።

“ማንም ቢሆን፤ በተለይ መንግሥታት የጋዜጠኞችን አንደበት እንዲዘጋ ሊፈቀድለት አይገባም” ብለዋል ላንሲንግ በዛሬው መግለጫቸው።

“ልክ ኻሾጊ እንደሚረዳው ሁሉ፤ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ ሚድያ ኤጀንሲም ያወቀ ዓለም ደኅንነቱ የተሻለ ዓለም እንደሆነ ይገነዘባል ­- ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃን ላንሲንግ ­- ዴሞክራሲ እንዲሠራም እንደዚያ ዓይነት ዓለም በቅድሚያ ሊኖር ይገባል” ብለዋል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG