ዋሺንግተን ዲሲ —
ዩኔስኮ ፀረ እሥራኤል አቋም ያለው ድርጅት በመሆኑ ራሴን ከአባልነት አገላለሁ ስትል ዩናይትድ ስቴትስ አስታወቀች።
ዩናይትድ ስቴትስ ድርጅቱ ውስጥ ከአባልነት ይልቅ በታዛቢነት ለመቆየት እንደምትፈልግ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሄዘር ናኦርተ ገልፀዋል።
ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳረጋገጠው፣ ዩናይትድ ስቴትስ እአአ ከታኅሣስ 22 ቀን ጀምሮ ነው አባልነቷ የሚቋረጠው።
የተመድ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ ለዩናይትድ ስቴትስ ውሳኔ፣ ቅሬታ የተመላበት መልስ ነው የሰጠው።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢሬና ቡኮቫ ባስተላለፉት መልዕክት፣
“የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሬክስ ቲለርሰን የዩናይትስ ስቴትስን ከድርጅቱ መለየት ሲገልፁልኝ፣ እንደ ዳይሬክተርነቴ፣ ጥያቄውን የተቀበልኩት በከፍተኛና ጥልቅ በሆነ ቅሬታ መሆኑን መግለጥ እወዳለሁ” ብለዋል።
ዩኔስኮ ፍልስጥኤማውያንን በአባልነት ሲቀበል፣ ዩናይትድ ስቴትስ ተቃውሞዋን ለማሳየት፣ የ2011 የአባልነት መዋጮዋን በከፍተኛ መጠን ቀንሳ መላኳ አይዘነጋም።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ