ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን ህግ ማስከበርና የሲቪሎች ደህንነት ድጋፍ የሚውል ሌላ ተጨማሪ የ447.5 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ማቀዷን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን ዛሬ አስታውቀዋል፡፡
ብሊንከን ዋሽንግተን ቀደም ሲል ለዩክሬን ከሰጠቸው የ187 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ጋር ዩክሬን ሰባት ወር ከቆየው የሩሲያ ወረራ ራሷን እንድትከላከልና፣ እንዲሁም ለዩክሬን ብሄራዊ ፖሊስና የመንግሥት ድንበር ጠባቂ አገልግሎት እንዲጠናከር የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥልበታለች ብለዋል፡፡
ያበረከትናቸው የግል መከላከያ መሳሪያዎች፣ የህክምና አቅርቦትና የጦር ተሽከርካሪዎች በዩክሬን ሲቪሎችና ተከላካዮቻቸው ላይ የሚደርሱትን አደጋዎች በከፍተኛ ደረጃ ቀንስዋል” በማለትም ተናግረዋል ብሊንክን፡፡
በቅርቡ ከተሰጠው አዲስ የገንዘብ እርዳታ ውስጥ የተወሰነው በዩክሬን ወታደሮችና ሲቪሎች ላይ አሰቃቂ ግፎችን የፈጸሙትንና በጦርነቱ የሞቱ በሺዎች የሚቆጠሩት ጋር በተያያዘ በሩሲያ ወታደሮች ላይ የሚደረገውን ምርመራ እንዲቀጥሉበት የሚውል መሆኑንም ብሊንከን አስረድተዋል፡፡
እርዳታውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ብሊንከን ባሰሙት ንግግር “ዩናይትድ ስቴትስ ከዩክሬናውያን ጎን በመቆም ዴሞክራቲክ ነጻና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ዩክሬንን ለመደገፍ ቁርጠኝነቷን ትቀጥልበታለች” ብለዋል፡፡