የፈረንሳይ መከላከያ ሚኒስትር ሴባስቲየን ለኮርኑ ሀገራቸው ለዩክሬን የስለላ መረጃ እያጋራች መሆኗን ዛሬ ሐሙስ ተናገሩ፡፡
ርምጃው ዩናይትድ ስቴትስ ከዩክሬን ጋራ የምታደርገውን የመረጃ ልውውጥ አቋርጫለሁ ማለቷን ተከትሎ የተሰማ ነው።
ርምጃው የተወሰደው የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች በብራሰልስ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በተገኙበት የመከላከያ ወጪያቸውን በማሳደግ እና ዩክሬን ከሩሲያ ጋራ በምታደርገው ጦርነት ድጋፍ ለመስጠት ቃል ስለ መግባት ውይይት ባደረጉበት በዛሬው ዕለት መሆኑ ነው፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከውይይቱ በፊት የአውሮፓ ኅብረት አባላት “ወደፊት ወሳኝ ርምጃዎችን እንደሚወስዱ” ተናግረዋል፡፡ በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን ስለምትሰጠው ድጋፍ በወሰደው የአቋም ለውጥ ስጋት ያላቸው መሆኑንም ማክሮን ገልጸዋ፡፡
"የአውሮፓ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በዋሽንግተን ወይም በሞስኮ መወሰን የለበትም" ብለዋል ማክሮን፡፡
ትረምፕ ባለፈው ሳምንት ከዘሌንስኪ ጋራ በኋይት ሀውስ ካደረጉት አወዛጋቢ ውይይት በኋላ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለኪቭ ተዋጊዎች የምትሰጠውን ወታደራዊ ርዳታ እንድታቆም በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ አዘዋል።
የየዩናይትድ ስቴትስ የማዕከላዊ ስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ጆን ራትክሊፍ ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለጊዜው የስለላ መረጃ ለኪቭ መረጃ ማጋራቷን ማቆሟን ትላንት ረቡዕ ተናግረዋል:: ሆኖም ዘሌንስኪ በኋይት ሀውስ ከትረምፕ ጋራ የነበራቸውን ልውውጥ “የሚጸጽት” በማለታቸውን እና ሀገራቸው ከሩሲያ ጋራ ለሚደረገው የሰላም ድርድር ዝግጁ መሆኗን በመናገራቸው የመረጃ ልውውጡ መቋረጥ ለረጅም ጊዜ ላይቆይ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
መድረክ / ፎረም