በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዛሬ በድንገት ዩክሬን ገብተዋል


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስቀድሞ ይፋ ባልተደረገ ጉብኝት ዛሬ ሰኞ ዩክሬን ገብተዋል፡፡ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች አንድ ዓመት ሊሞላ ጥቂት ቀናት በቀሩበት ባሁኑ ወቅት ወደኪቭ የተጓዙት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት የተጓዙት “ ለዩክሬን ነጻነት፡ ለሉዐላዊነቷ እና የግዛት አንድነቷ ያለንን ድጋፍ ለመግለጽ ነው” ብለዋል፡፡

ባይደን በኪየቭ በማሪንሲ ቤተ መንግሥት ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ጎን ሆነው ባደረጉት ንግግር ዩናይትድ ስቴትስ የመድፍ ተተኳሾች እና ጸረ ታንክ መሳሪያዎችን ጨምሮ የ500 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ዕርዳታ እንደምትሰጥ ይፋ አድርገዋል፡፡ “በዚህ ሳምንት በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንጥልባታለን” ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

ባይደን በንግግራቸው የዩክሬንን የጦር ኅይል የሚረዱ ከሀምሳ የሚበልጡ ሀገሮች ያሉበት ቅንጅት እየተፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ትላልቆቹ ኢኮኖሚዎች በሩስያ ላይ ካሁን ቀደም ታይቶ በማያውቅ ደረጃ የኢኮኖሚ ቅጣት እንዲጥሉ የማስተባበር ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑም አውስተዋል፡፡

“ ፑቲን ዩክሬን የተዳከመች፡ ምዕራባውያኑ የተከፋፈሉ መስሏቸው የሚያሸንፉን መስሏቸው ነበር” ያሉት ባይደን “ አሁን ግን እንደዚያ የሚያስቡ አይመስለኝም” ብለዋል፡፡

ዘሌንስኪ በበኩላቸው “ዩክሬን ትልቅ ግምት በምትሰጠው በዚህ ወቅት ፕሬዚደንት ባይደን በመምጣታቸው አመሰግናለሁ” ብለው ስለጦርነቱ ይዞታ ከዩናይትድ ስቴትሱ መሪ ጋር ለመወያየት በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

በዋና ከተማዋ እና በሌሎችም የዩክሬን አካባቢዎች ፕሬዚደንት ባይደን እና ዜሌንስኪ ኪየቭ የሚገኘውን ካቴድራል በመጎብኘት ላይ እያሉም ጭምር የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያዎች ተሰምተዋል፡፡ ፕሬዚደንት ባይደን እና ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ በጦርነቱ በወደቁ ጀግኖች መካነ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን አስቀምጠዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ባይደን ጉብኝት ቀደም ብሎ የታቀደ ቢሆንም ከኋይት ሐውስ የተሰጠው ይፋ መግለጫ ያመለከተው ግን ዛሬ ማታ ከዋሽንግተን እንደሚነሱ እና መጀመሪያ የሚጓዙትም ወደፖላንድ እንደሚሆን ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን በመጪው ረቡዕ ወደዋሽንግተን ከመመለሳቸው አስቀድመው ከኔቶ ዋና ጸሐፊ ዬንስ ስቶልትንበርግ እንዲሁም የቡካሬስቱ ዘጠኝ ሀገሮች ስብስብ መሪዎች ጋር እንደሚነጋገሩ ኋይት ሐውስ ትናንት ያወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን እና የመከላከያ ሚንስትር ሎይድ ኦስተንን ጨምሮ የባይደን አስተዳደር ባለስልጣናት ባለፈው ዓመት ውስጥ ዩክሬንን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡ ቀዳማዊት ዕመቤት ጂል ባይደንም ባለፈው ግንቦት በድንገት ዩክሬንን ጎብኝተዋል፡፡ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪም ባለፈው ታህሳስ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የመጀመሪያቸው በሆነው የውጭ ሀገር ጉዞአቸው ዋሽንግተንን ጎብኝተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቻይና ዩክሬን ውስጥ ለሚዋጉ የሩስያ ኅይሎች የገዳይ መሣሪያ ዕርዳታ ከሰጠች በውል ይህ ነው ብለው ያልገለጹት አጸፋ እንደሚከተላት ዛሬ ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ህብረት አስጠንቅቀዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን “በዩናይትድ ስቴትስ እና በቻይና ግንኙነት ላይ ተጨባጭ መዘዝ ይከተላል” ያሉ ሲሆን የዩናይትድ ስቴትስን ሥጋት በቀጥታ ለዋናው የቻይና የውጭ ፖሊሲ ባለሥልጣን ዋንግ ዪ አሳውቄአቸዋለሁ ብለዋል፡፡

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን በበኩላቸው ዛሬ በአንድ ገለጻ ላይ በሰጡት ቃል ዩናይትድ ስቴትስ ቻይናን እንዲህ ያለውን ጥያቄ ልትጠይቃትአትችልም ብለው ቻይና ከሩስያ ጋር ያላት ግንኙነት የገለልተኝነት ያለመፋጠጥ እና ስስተኛ ወገንን ዒላማ ያለማድረግ መርሆችን የተከተለ ነው” ብለዋል፡፡ አስከትለውም ያለማቋረጥ ወደ ውጊያ ሜዳ የጦር መሳሪያ የምትልከው ዩናይትድ ስቴትስ እንጂ ቻይና አይደለችም” ብለዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አእቀባዩን እንዳነጋገሯቸው እና ሀገራቸውለሩስያ መሳሪያ እንዳትሰጥ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG