በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ በሙስና እና በመብት ረገጣ በተወነጀሉ የዩጋንዳ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጣለች


ፎቶ ፋይል፦ የዩጋንዳ ፓርላማ አፈ ጉባኤ አኒታ አሞንግ ካምፓላ፤ ዩጋንዳ እአአ ግንቦት 2/2023
ፎቶ ፋይል፦ የዩጋንዳ ፓርላማ አፈ ጉባኤ አኒታ አሞንግ ካምፓላ፤ ዩጋንዳ እአአ ግንቦት 2/2023

ዩናይትድ ስቴትስ በሙስና አድራጎት ወይም በሰብዓዊ መብት ጥሰት በተወነጀሉ አምስት የዩጋንዳ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ እንደምትጥል ዛሬ ሐሙስ አስታወቀች፡፡ በመጠነ ሰፊ የሙስና ተግባር ምክንያት የጉዞ ዕገዳ ከሚጣልባቸው አራት ባለስልጣናት መካከል አንዷ ባለፈው ወር ብሪታኒያ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰደችባቸው የዩጋንዳ ፓርላማ አፈ ጉባኤ አኒታ አሞንግ መሆናቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል፡፡

በድህነት የተጎዳው የዩጋንዳ የድንበር ግዛት ካራሞጃ ሚንስትሮች የነበሩት ሜሪ ጎሬቲ ኪቱቱ እና አግነስ ናንዱቱ እንዲሁም የቀድሞ የፋይናንስ ሚኒስትር ደኤታ አሞስ ሉጎሎቢ ማዕቀብ ከሚጣልባቸው ባለስልጣናት መካከል መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ባወጡት መግለጫ “ሦስቱ ሰዎች የመንግሥት ሐብት ያለአግባብ አውለዋል በከፋ ድሕነት ለሚኖሩ ማሕበረሰቦች የሚገባ ቁሳቁስ ወደሌላ አዛውረዋል” ብለዋቸዋል፡፡ ባለስልጣናቱ “የመንግሥት ሥልጣናቸውን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል” ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡

ቀድሞ የዩጋንዳ የመከላከያ ኅይሎች ምክትል አዛዥ የነበሩት ፒተር ኤልዌሉም “በፈጸሟቸው እጅግ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል” ያሉት የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ የመከላከያ ኅይሎች አዛዥ በነበሩበት ወቅት በመከላከያ ኅይሎቹ በተፈጸሙ የዘፈቀደ ግድያዎች ተሳትፈዋል ብለዋቸዋል፡፡ በተዘረዘሩት የተጠቀሱት የዩጋንዳ ባለስልጣናት በተዘረዘሩት አድራጎቶቻቸው ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ መታገዳቸውን ማቲው ሚለር አስታውቀዋል፡፡

የሐገሪቱን የዲሞክራሲ ሂደት በማደናቀፍ እና የተገለሉ እና ተጋላጭ የሆኑ ማሕበረሰቦችን በማፈን ተግባር በተወነጀሉ ሌሎችም በርካታ የዩጋንዳ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ዕገዳ ለመጣል ዕቅድ መኖሩን ቃል አቀባዩ አክለው አመልክተዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG