ዋሽንግተን የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፍ ልማት ተራድዖ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ከትላንት ሰኞ ጀምሮ ሥራ እንዳይገቡ ታዝዘዋል።
መመሪያው ለሠራተኞቹ የተሰጠው ትላንት ሰኞ ሲሆን በፕሬዝደንቱ ፈቃድ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን አሠራር እንዲመረምሩ ልዩ ኅላፊነት የተሰጣቸው ቢሊዮነሩ ኢላን መስክ "መሥሪያ ቤቱ እንዲዘጋ ፕሬዝደንቱ ተስማምተዋል" ብለው ማስታወቃቸውን ተከትሎ እንደሆነ ተመልክቷል። መስክ ትላንት ማለዳ በኤክስ ማኅበራዊ መገናኛ የቀጥታ ውይይት መድረክ ኤክስ ስፔስ ላይ ሲናገሩ "ከፕሬዝደንቱ ጋር ስድስት አስርት ዓመታት ስላስቆጠረው ተቋም ስንወያይ መዘጋት እንዳለበት ተስማምተዋል" ብለዋል።
መስክ" ተቋሙ አንድ ትል ያለበት አፕል ሳይሆን እንዳለ በትላትል የተወረሰ በመሆኑ ሊጠገን ስለማይችል መወገድ ነው ያለበት። እንዘጋዋለን" ማለታቸው ተጠቅሷል።
የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ተራድዖ ድርጅት (ዪ ኤስ ኤ አይ ዲ) 120 በሚሆኑ ሀገሮች የሚካሄዱትን የሰብዐዊ ርዳታ፥ የልማት እና የጸጥታ መርሀ ግብሮች የሚቆጣጠር ሲሆን ኢላን መስክ፥ ፕሬዚደንት ትረምፕ እና አንዳንድ ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባላት ለዘብተኛ (ሊበራል ) ዓላማዎችን ያራምዳል ብለው አጥብቀው በመወንጀል አነጣጥረውበታል ።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለኢላን መስክ ተቆጣጣሪዎች በሚስጥር መያዝ ያለባቸው የተቋሙን መረጃዎች ወደሚቀመጥባቸው የተከለከሉ ሥፍራዎች እንዳይገቡ የከለከሉ ሁለት የተቋሙ ከፍተኛ የደኅንነት ባለሥልጣናት በፕሬዝደንት ትረምፕ ትዕዛዝ በዕረፍት ከሥራ ውጪ መደረጋቸውን የተቋሙ የአሁን እና የቀድሞ ባለሥልጣናት ለአሶሽየትድ ፕረስ አመልክተዋል።
የትረምፕ አስተዳደር በፌዴራሉ መንግሥት እና በበርካታ መርሀ ግብሮቹ ላይ አጠናክሮ በቀጠለው ዘመቻ የበረታ ትኩረት ካደረገባቸው ተቋማት አንዱ የሆነው ዩ ኤስ ኤድ ዌብሳይቱ ቅዳሜ እለት ካለምንም ማብራሪያ በድንገት እንዲነሳ ተደርጓል።
ትረምፕ እሁድ ማታ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል " ሲመራ የቆየው በጽንፈኛ የአዕምሮ ሕመምተኞች ነበር ፥ እናስወጣቸዋለን" ብለዋል።
በተያያዘ ሌላ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ የተቋሙን ተጠባባቂ አስተዳዳሪነት እሳቸው መያዛቸውን አስታውቀዋል።
መስክ እና ትረምፕ ድርጅቱን በሚመለከት የተናገሩት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ በሚንስትርነት የመጀመሪያቸው በሆነው የውጭ ሀገር ጉዞ በላቲን አሜሪካ ጉብኝት ላይ ሳሉ ነው። ሩቢዮ የዓለም አቀፍ ርዳታ ተቋሙን የመዝጋት ዕቅድ ስለመኖሩ ተናግረው አያውቁም።
የትረምፕ አስተዳደር እና ሩቢዮ ዩናይትድ ስቴትስን የውጭ ርዳታ ከአሁን ቀደም ታይቶ በማያውቅ መጠን ማቋረጣቸውን ተከትሎ እብዛኛው የዓለም አቀፍ ልማት ርዳታ ተቋሙ መርሃ ግብሮች ቆመዋል። በዚህም የተነሳ የረድዔት ድርጅቶች በሺዎች የተቆጠሩ ሠራተኞቻቸውን ለማሰናበት ተገድደዋል። የተቋሙ የዋሽንግተን ቢሮ አመራሮች እና ሠራተኞች በጊዜያዊነት ከሥራ ውጭ ሆነዋል።
ተቋሙ የተዘጋበትን ትዕዛዝ ያስፈጸሙት በመጀመሪያው የትረምፕ አስተዳደር የፖለቲካ ተሹዋሚ የነበሩት እና በአሁኑም የተመለሱት ፒተር ማሮኮ ናቸው። የድርጅቱ ሠራተኞች የጎብኚ መታወቂያ አድርገው በተቋሙ ውስጥ እየተዘዋወሩ ጥያቄ የሚጠይቁት የተቋሙ ሠራተኛ ያልሆኑ ሰዎች "ዶዥ" በሚል የምህጻር ስም የሚጠራው የኢላን መስክ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ተቆጣጣሪ አካል ሰዎች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ይጠረጥራሉ።
ዲሞክራት የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ፕሬዚደንቱ ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ ተቋሙን ለመዝጋት ህገ መንግሥታዊ ሥልጣን የላቸውም ብለዋል።
መድረክ / ፎረም