ዋሺንግተን ዲሲ —
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ኮቪድ-19 ጉዳት ላደረሰባቸው አሜሪካውያን እንዲሰጥ የጠየቁትና የዩናይትድ ስቴትስ ምክርቤት ያፀደቀውን ለግለሰቦች የሚሰጥ የ2 ሺህ ዶላር የክፍያ ዕቅድ ዲሞክራቶች ማክሰኞ ወደ ሴኔት ይመሩታል።
ዲሞክራቶች አናሳ በሆኑበትና የሴኔቱ አብላጫ ፓርቲ መሪ ሚች ማክኔል እቅዱን ለምርጫ ለማቅረብ ምንም ምልክት ባላሳዩበት ሁኔታ ተሰሚነት ያላቸው የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላቱ ወደ ድርጊት እንዲሄድ የሚያስገድዱ የተለያዩ አማራጮችን ይጠቀማሉ ተብሏል።
ማንኛውም የሴኔቱ አባል ተቃውሞ ካቀረበ ሊቆም የሚችለውን እንቅስቃሴ የጀመሩት የአናሳው ዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ቸክ ሹመር ለአስቸኳይ ጊዜ የሚሰጠው ድጋፍ 2 ሺህ ዶላር እንዲሆን በሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ሰዎች ይደግፋሉ ብለዋል። በሰኔቱ ያሉ ሪፐብሊካኖች የአሜሪካን ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸውን ፍላጎት ሊያሟላ የሚችልን ድጋፍ እንዳያቆም ሚች ማክኔል ሊያረጋግጡ ይገባል ሲሊም ተናግረዋል።