በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ ላሰቡ አሜሪካውያን ዜጎቿ ቀደም ሲል አውጥታው የነበረውን የጉዞ ማስጠንቀቂያ አራዘመች


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጥቅምት 11 የወጣውን የሚተካ የጉዞ ማስጠንቀቂያ እንደሆነ በመግለፅ ባወጣው አዲስ የጉዞ ማስጠንቀቂያ፤ በኢትዮጵያ በሕዳር ወር 2008 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ጸረ መንግሥት ዐመጽና ዓመጹን ተከተሎ የተፈጠረው የፀጥታ ሁኔታ ወዴት እንደሚያመራ መተንበይ አስቸጋሪ በመሆኑን የአሜሪካ ኤምባሲ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ሊቋረጥ ስለሚችል ቀደም ሲል የተሰጠው የጉዞ ማስጠንቀቂያ እንደሚቀጥል አሳስቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጥቅምት 28/2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሆነውን ያስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ደንግጓል። ጥቅምት 4 በወጣ መመሪያም ግለሰቦች መገናኛ ብዙኃንን ሲከታተሉ በስብሰባዎች ላይ ሲካፈሉ፣ ከባዕዳን መንግሥታት ወይም ድርጅቶች ጋር ሲገናኙ እንዲሁም የሰዓት እላፊ ገደቡን ጥሰው ቢገኙ ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ተይዘው ሊታሠሩ እንደሚችሉ ያብራራል።

መመሪያው በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት የዩናይትድ ስቴትስን ዜጎች ሲያስር መታሰራቸውን ለአሜሪካ ኤምባሲ ተከታታይነት ባለው ሁኔታ እንደማያሳውቅ ጠቁሟል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሙሉ ቃል የእንግሊዝኛ ቅጂ በዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ዌብሳይት ላይ ይገኛል፡፡

የኢንተርኔትና የሞባይል ስልክ አገልግሎቶች በመላ ሃገሪቱ ያለማስጠንቀቂያም በየወቅቱ ስለሚቋረጡና ሙሉ በሙሉም ስለሚዘጉ ሁኔታው አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዜጎቹን የመርዳት አቅሙን እንደሚያደናቅፍ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ማስታወቂያ አብራርቷል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች አማራጭ የግንኙነት ዘዴዎች እንዲኖሯቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኖሩ እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሊያጋጥም የሚችል መሆኑን ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸውን እንዲያሳውቁ ማስታወቂያው መክሯል፡፡

ዜጎቹ ከሰላማዊ ሰልፎችና ሰዎች በብዛት ከሚሰበሰቡባቸው አካባቢዎች እንዲርቁ፤ የሚገኙባቸውን ሥፍራዎች ያለማቋረጥ እንዲያጠኑ፤ የግላቸው ደኅንነት ያለበትን ሁኔታም በአንክሮ እንዲገመግሙ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በዚሁ የጉዞ ማስጠንቀቂያው ማራዘሚያ ማስታወቂያ ላይ አሳስቧል፡፡

መንግሥቱ ሰላማዊ ሠልፎችን ለመበተን ሰዎች ላይ በቀጥታ ሊተኩስ እንደሚችል፣ ሰላማዊ ሊሆኑ ለታሰቡና ለሚጠሩ ሰልፎች የኃይል ምላሽ እንደሚሰጥና ሰልፎቹ ያለማስጠንቀቂያ ወደ ሁከትነት ሊለወጡ እንደሚችሉ ዜጎቹ ማስታወስ እንደሚኖርባቸው የጠቆመው ይህ መልዕክት የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች የደኅንነት ሁኔታቸውን እየተከታተሉ አስፈላጊ ከሆነም ፈጥነው ከሃገር መውጣት የሚያስችላቸውን የአደጋ ጊዜ ዕቅዶች እንዲያዘጋጁ መክሯል፡፡

“ኢትዮጵያ ውስጥ የምትኖሩ ከሆነ ወይም ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ እያሰባችሁ ከሆነ በተለይ ኢትዮጵያን በሚመለከተው መረጃ ላይ ከሰፈረው የደኅንነት (Safety and Security) ክፍል ላይ ተጨማሪና ጠቃሚ መረጃ አግኙ” ይላል ይኸው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መግለጫ፡፡

ሃገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለመተንበይ ወይም የሚመጣውን ለመገመት አስቸጋሪ እንደሆነ የሚናገረው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች “ስቴፕ” በሚል ምኅፃረቃል በሚጠራው ስማርት ትራቭለር ኢንሮልመንት ፕሮግራም” (Smart Traveler Enrollment Program (STEP) ከመመዝገባቸው በተጨማሪ የደኅንነት መረጃዎችን በስልክና በቴክስት ማግኘት እንዲችሉ የስልክ ቁጥሮቻቸውን እንዲያስመዘግቡ በጥብቅ እንደሚያሳስብ አስታውቋል፡፡

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ለተጨማሪ መረጃ የሚረዱ አድራሻዎችንም አስፍሯል፡፡

For further information:

XS
SM
MD
LG