የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ አራተኛ ወሩን ያስቆጠረውን የሩሲያ ወረራ በመመከት ላይ የምትገኘው ዩክሬንን ለማገዝ፣ የላቁ ተጨማሪ የሮኬት መሳሪያዎችና ጥይቶችን ለመስጠት መወሰናቸውን ትናንት ማክሰኞ ተናገሩ፡፡
ባይደን ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ባሰፈሩት የአስተያየት ጽሁፋቸው፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩክሬንን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ውጊያ፣ ያላትን አቋም እንድታጠናክር መሳሪያና ጥይቶችን የረዳች ሲሆን፣ በሂደትም ከሩሲያ ጋር ለምታደርገው የሰላም ድርድር ድጋፏን ትሰጣለች ብለዋል፡፡
ባይደን “ያለምንም ምክንያት በተፈጠረ ጠብ ጫሪነት፣ የማወለጃ ሆስፒታሎች እና የባህል ማዕከላትን በቦምብ መደብደብና እንዲሁም ሚሊዮኖች እንዲፈናቀሉ ያስገደደው የዩክሬኑ ጦርነት ትልቅ የሞራል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው” ሲሉ ጽፈዋል፡፡
የላቁ መሳሪያዎቹን የመላኩ ውሳኔ የተገለጸው ቀደም ሲል በባይደን አስተዳደር ማንገራገር መኖሩ ከታየ በኋላ ነበር፡፡ ባይደን ባለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያ ድረስ ዘልቀው፣ ሩሲያን ሊመቱ የሚችሉ ሮኬቶችን የመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸው ነበር፡፡
“ከሚስተር ፑትን የማልግባባውን ያህል፣ ድርጊታቸው እጅግ በጣም የሚያስቆጣም ቢሆን ዩናትይትድ ስቴትስ እሳቸውን ከሞስኮ የማስወገዱን ሀሳብ አትሞክረውም” ያሉት ባይደን “ዩናይትድ ስቴትስ ወይም አጋሮቻችን እስካልታጠቁ ድረስ በዚህ ግጭት ዩክሬን ውስጥ ያሉ የሩሲያ ወታደሮችን የሚወጉ የአሜሪካ ወታደሮችን በመላክም ሆነ በቀጥታ ተካፋይ አንሆንም ዩክሬናውያን ከድንበራቸው ተሻግረው ጥቃት እንዲሰነዝሩም አንፈቅድም፡፡” ብለዋል፡፡
አንድ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለአሶሼይትድ ፕሬስ ትናንት እንደተናገሩት እስከ 70 ኪሜ ሊጓዙ የሚችሉ መካከለኛ ርቀት ያላቸው ሮኬቶችን ጨምሮ አዲስ የሚሰጡት መሳሪያዎች ዝርዝር ዛሬ ረቡዕ ሊገለጽ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡