በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ካጋሜ ለመጭዎቹ ሃያ ዓመታት ሥልጣን ላይ ሊቆዩ ይችላሉ


ዩናይትድ ስቴትስ ቅሬታና ሥጋቷን ገልፃለች፡፡

የርዋንዳ ህገመንግሥት ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን መወዳደር እንዲችሉ እንዲፈቅድ ሆኖ እንዲለወጥ የሃገሪቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ወሰነ፡፡

ሃሣቡ ከዚህ በኋላ ለውሣኔ-ሕዝብ የሚቀርብ ሲሆን በቀላሉ ሳያልፍ አይቀርም ተብሎ ተገምቷል፡፡

ማርግሬት ኒያጋሁራ የሚባሉ እንደራሴ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ምክር ቤቱ በውሣኔው የጠበቀው ፕሬዚዳንት ካጋሜ ለሦስተኛ ዘመን እንዲመሩ የሃገሪቱ የ 3.6 ሚልዮን መራጮች ያሳዩትን ፍላጎት ነው ብለዋል።

እነዚህ ድምፅ የመስጠት መብት ያላቸው ዜጎች ፕሬዚዳንት ካጋሜ ለሦስተኛ ጊዜ እንዲመረጡ ለማስቻል ሕገ-መንግሥቱ እንዲቀየር “ፊርማ አሰባስበው” ለምክር ቤቱ ጥያቄ አቅርበዋል ሲሉ የምክር ቤት አባሏ ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።

“ሀገሪቱ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ያለፈች በመሆኗ የአዲስ መሪዎች ሙከራ አያስፈልጋትም” ሲሉም አክለውበታል።

“ሀገሪቱ ወዳለፈው ፍጅትና ትርምስ የማትመለስበት ደረጃ ላይ መድረሷ እስኪረጋገጥ ድረስ ሰዎች ፕሬዚዳንት ካጋሜ ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ይፈልጋሉ” ብለዋል ማርግሬት ኒያጋሁራ።

አሁን ባለው የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት የሁለተኛ ዘመን ሥልጣናቸው እአአ በ 2017 ዓ.ም ማብቃት አለበት።

ይሁንና ህገ-መንግስቱ እንዲሻሻል በቀረበው የውሣኔ ሃሣብ መሠረት ለሌላ የሰባት ዓመታት የስልጣን ጊዜ ለመወዳደር ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ደግሞ ለሁለት የአምስት ዓመታት የሥልጣን ዘመናት ተወዳድረው ሊያሸንፉ ይችላሉ።

በዚህ መሠረት ካጋሜ እአአ እስከ 2034 ዓ.ም ድረስ ለተጨማሪ አሥራ ሰባት ዓመታት ሥልጣን ላይ ሊቆዩ ይችላሉ እየተባለ ነው፡፡

የርዋንዳ ዲሞክራያዊ አረንጓዴ ፓርቲ የሚባለው ተቃዋሚ ድርጅት የሕገ-መንግሥቱ ማሻሻያ “ለዘላቂ ሰላምና ለፀጥታ ፈተና ይሆናል” ሲል ነቅፏል።

ርዋንዳ ከዩናይትድ ስቴትስ የቅርብና ወዳጅ ሃገሮች አንዷ ብትሆንም አሜሪካ ፖል ካጋሜ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ለመወዳደር መሞከር የላባቸውም ብላ እንደምታምን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ቃል አቀባይ ማርክ ቶነር ትናንት ተናግረዋል፡፡

“ፕሬዚዳንት ካጋሜ የርዋንዳን አዲስ የመሪዎች ትውልድ ለማጠናከር ቀደም ሲል በገቡበት ቁርጠኝነት ይፀናሉ፤ በዚህም የአሁኑ የሥልጣን ዘመናቸው እአአ በ1917 ዓ.ም ሲያበቃ ይለቅቃሉ ብለን እንጠብቃለን” ብለዋል ቶነር፡፡

ካጋሜ ሥልጣኑ ላይ የሙጥኝ ብለው የሚቀጥሉ ከሆነ ዩናይትድ ስቴትስ ልትወስድ የምትችላቸው እርምጃዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ አልተናገሩም፡፡ ዘገባውን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።

ካጋሜ ለመጭዎቹ ሃያ ዓመታት ሥልጣን ላይ ሊቆዩ ይችላሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:47 0:00

XS
SM
MD
LG