በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ያቋረጠችውን የምግብ ርዳታ ሥርጭት ልትጀምር ነው


ፎቶ ፋይል - የዓለም የምግብ ፕሮግራም ወደ ትግራይ የዕርዳታ ቁሳቁስ ለማጓጓዝ በማይ ፀብሪ ከተማ፣ እእአ ሰኔ 26/2021
ፎቶ ፋይል - የዓለም የምግብ ፕሮግራም ወደ ትግራይ የዕርዳታ ቁሳቁስ ለማጓጓዝ በማይ ፀብሪ ከተማ፣ እእአ ሰኔ 26/2021
ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ አቋርጣው የነበረውን የርዳታ ምግብ የማከፋፈል ሥራ አንድ እንደምትጀምር ዛሬ አስታወቀች። ርዳታውን፣ አንድ ሚሊዮን ለሚደርሱ ተረጂዎች ብቻ በማደል እንደሚጀመር፣ ዩናይትድ ስቴትስ ገልጻለች፡፡
ይህም ኾኖ የምግብ ርዳታው፣ በተቀነባበረ መንገድ ከታለመለት ዓላማ ውጭ መዋሉ መረጋገጡን ተከትሎ ዕደላው በተቋረጠባቸው አብዛኞቹ አካባቢዎች፣ አሁንም እንደማይቀጥል ታውቋል።
የርዳታ ምግብ ዕደላው በፍጥነት የሚጀመረው፥ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሶማሊያ እና ከኤርትራ ተሰደው በኢትዮጵያ በሚገኙት 28 የስደተኛ ካምፖች ውስጥ ለተጠለሉ ስደተኞች እንደኾነ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አመልክታለች።
በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት ከተካሔደው አሠቃቂ ጦርነት በማገገም ላይ በሚገኙት አካባቢዎች ይሰጥ የነበረው የምግብ ርዳታ፣ ከታለመለት ዓላማ ውጭ የሚውልበትን አሠራር ለማስቆም የሚያስችሉ ርምጃዎች ተግባራዊ ማድረግ እስኪቻል ድረስ እንደተቋረጠ እንደሚቆይ ተገልጿል።
“የምግብ ዋስትና ችግር ላለባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የምናደርገው ድጋፍ፣ ለታለመላቸው ተጠቃሚዎች ብቻ እንደሚደርስ ማረጋገጫ እስክናገኝ ድረስ እንደተቋረጠ ይገኛል፤" ሲሉ፣ የዩናይትድ ስቴትሷ የዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት ቃል አቀባይ ጄሲካ ጄኒን ተናግረዋል።
"ድርጅቱ ቅድሚያ የሚሰጠው፣ በሁሉም ክልሎች ለተቸገሩ ወገኖች በተቻለ ፍጥነት የምግብ ርዳታ እደላውን ማስቀጠል ነው። በመኾኑም፣ አስተማማኝ የአሠራር ለውጥ ተግባራዊ እንደተደረገ ሥራውን ለመጀመር ዝግጁ ነን፤" ብለዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በተመሳሳይ ምክንያት ከአራት ወራት በፊት አቋርጦት የነበረውን የምግብ ርዳታ ዕደላ፣ ቀስ በቀስ መጀመሩን ከዚኽ ቀደም ማስታወቁን መዘገባችን አይዘነጋም። በአንዳንድ ቦታዎች በአነስተኛ መጠን ርዳታ በማከፋፈል ላይ እንደኾነ የገለጸው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ መንግሥት፣ አሁንም በሒደቱ ውስጥ ሚና አለው፤ ብሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG