ቲክቶክ በአሜሪካ ጥቅም ላይ እንዳይውልም ሆነ በሽያጭ እንዳይተላለፍ የወጣውን ሕግ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የሚገኝ የፌዴራል የይግባኝ ፍርድ ቤት ደግፏል። ውሳኔው ቲክቶክ በጥቂት ወራት ውስጥ በአሜሪካ እንዲታገድ ሊያስደርግ ይችላል ተብሏል።
ቲክቶክ በአሜሪካ በአገልግሎት ላይ ውሎ ለመቆየት በሚያደርገው የሕግ ፍልሚያ ትልቅ ሽንፈት ነውም ተብሏል።
ሕጉ፤ ቲክቶክ መሠረቱን ቻይና ካደርገውና ባይትዳንስ ከተሰኘው እናት ኩባንያ እስከሚቀጥለው ወር አጋማሽ ድረስ እንዲገነጠል ካለዛ ግን እንደሚታገድ ይደነግጋል።
ፍርድ ቤቱ፣ ቲክቶክን ለማገድ የወጣው ሕግ ሕገ-መንግስታዊ ነው ሲል የማሕበራዊ ሚዲያውን ሃሳብን በነፃ የመግለጽ መብት ሙግት ውድቅ አድርጓል።
የቲክቶክ እናት ኩባንያ ከቻይና መንግስት ጋራ ግንኙነት አለው፣ በመሆኑም የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው በሚል የወጣውን ሕግ፣ ፕሬዝደንት ባይደን በፊርማቸው ያጸደቁት ባለፈው ሚያዚያ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ቲክቶክን ሊያግዱ የሞከሩት ዶናልድ ትረምፕ፣ በቅርቡ በተደረገው ምርጫ ዘምቻዎቻቸው ወቅት የቲክቶክን መታገድ እንደሚቃወሙና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩን ለማዳን እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ሁለቱ ከሳሾች ቲክቶክና ባይትዳንስ የፌዴራል ፍ/ቤቱን ውሳኔ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደሚሉ የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም