በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዋሺንግተን ኢራንን ያግዛል ባለችው መረብ ላይ ማዕቀብ ጣለች


ፎቶ ፋይል፦ የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ግምጃ ቤት
ፎቶ ፋይል፦ የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ግምጃ ቤት

ኢራን ድፍድፍ ዘይትና የዘይት ተዋፅዖ ምርቶቿን ምሥራቅ እስያ ውስጥ እንድትሸጥ አግዟል ስትል ዩናይትድ ስቴትስ በከሰሰችው አንድ የቻይናና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የንግድ ተቋማት መረብ ላይ ዛሬ ማዕቀብ ጥላለች።

ዋሺንግተን እርምጃውን የወሰደችው ኢራንን የዛሬ ሰባት ዓመት ወደ ተፈረመው የ2015ቱ የኒኩሌር ስምምነት እንድትመለስ ለማስገደድ በያዘችው ጥረት ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

በነጋዴ ግለሰቦችና በተለያዩ የንግድ ተቋማት የተዘረጋው መረብ መሠረታቸውን ፋርስ ባህረ ሰላጤ ያደረጉ የግንባር ኩባንያዎችን የሚያገናኝ ሌላ መረብ እየተጠቀመ በብዙ ሚሊዮኖች ዶላሮች የሚገመቱ ምርቶችን ከኢራን ድርጅቶች ወደ ቻይና እና ሌሎች የምሥራቅ እስያ ሃገሮች እንዲደርሱና ለገበያ እንዲቀርቡ እንደሚያደርግ የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ዋሺንግተን በኢራን ፔትሮኬሚካል ምርቶች ወጭ ገበያ ላይ የተሰማሩ የቻይና ኩባንያዎችን ዒላማ ማድረጓን ያጠናከረችው የኒኩሌር ስምምነቱን የማደስ ተስፋ እየተመናመን በመምጣቱ እንደሆነ እየተዘገበ ነው።

ስምምነቱን ከመክሰም ለማትረፍ በሚል ባለፈው ሣምንት ካታር ዋና ከተማ ዶሃ ላይ በቴህራንና በዋሺንግተን መካከል የተደረገው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ኢራን በኒኩሌር መርኃግብሯ ላይ ሙጥኝ በማለቷ ምክንያት ያለ ስኬት ተበትኗል።

ከ2015ቱ ስምምነት በተናጠል መውጣታቸውን የያኔው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ የዛሬ አራት ዓመት ካሳወቁና ከኢራን ላይ ተነስተው የነበሩ ማዕቀቦችን መልሰው ከጣሉ በኋላ ቴህራን ለሰላማዊ ጉዳይ እንደያዘችው የምትናገረውን መርኃግብሯን አጠናክራ መቀጠሏና እንዲያውም የዓለምአቀፍ አቶሚክ ኢነርጂ ግዴታዎቿንም እየጣሰች እንደሆነ ተነግሯል።

XS
SM
MD
LG