በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአሜሪካ መንግሥት እና በጉግል ኩባንያ መካከል የፍ/ቤት ክርክር ተጀምሯል


የኩባንያው ካምፓስ ውስጥ ባለ ህንፃ የጉግል አርማ፤ ማውንቴን ቪው፣ ካሊፎርኒያ፤ እአአ መስከረም 24/2019
የኩባንያው ካምፓስ ውስጥ ባለ ህንፃ የጉግል አርማ፤ ማውንቴን ቪው፣ ካሊፎርኒያ፤ እአአ መስከረም 24/2019

በኢንተርኔት የአሠሣ ሥርዐቱን “ብቻውን ተቆጣጥሯል” በሚል፣ የአሜሪካ መንግሥት በጉግል ኩባንያ ላይ የመሠረተው ክሥ፣ ዛሬ፣ በዋሽንግተን ዲሲ ባለ ፍርድ ቤት መታየት ጀምሯል።

በፍትሕ መ/ቤቱ ጠበቃ የኾኑት ኬኔት ዲንዘር እንደተናገሩት፣ ክሡ፥ የወደፊቱን የኢንተርኔት ዕጣ ፈንታ የሚጠቁምና ጉግል ክብደት ያለው ተፎካካሪ ይመጣበት እንደኹ ያመላክታል፡፡

ለሚቀጥሉት 10 ሳምንታት፣ ክሡን የሚያስረዱ ከ100 በላይ ምስክሮች ይደመጣሉ፡፡ ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ፣ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ የከፈተው ክሥ ተገቢነት እንደሌለው፣ አስቻይ ዳኛ አሚት ሜታን ለማሳመን ይሞክራል፤ ተብሏል።

በዋሽንግተን ዲስ እየታየ ያለው ክሥ፣ ከ20 ዓመታት በፊት፣ “የዊንዶውስ የኮምፒውተር ሥርዐትን በብቸኝነት ተቆጣጥሯል፤” ሲል፣ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ በማይክሮሶፍት ኩባንያ ላይ ካቀረበው ወዲህ፣ በአንድ ግዙፍ ኩባንያ ላይ የተከፈተ ከባድ ክሥ እንደኾነ ተነግሯል።

የጉግል ኩባንያ፣ “ከኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ አምራቾች፣ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ሰጪዎች እና ከሌሎችም ኩባንያዎች ጋራ ልዩ ኮንትራት በመፈጸም፣ በኢንተርኔት የአሠሣ ሥርዐቱን በበላይነት ተቆጣጥሮ፣ ሌሎች በአማራጭነት እንዲታዩ ዕድል አልሰጠም፤” ሲል መንግሥት ይከራከራል።

በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር፣ ለአፕል እና ለሌሎችም ኩባንያዎች በመክፈል፣ በስልኮች እና በድረ ገጽ መፈለጊያዎች ላይ ጉግል ቀድሞ የሚመጣ አሣሽ እንዲኾንና በተለይ ሌሎች ጀማሪ የመፈለጊያ ኩባንያዎች፣ ለማደግ ዕድል እንዳያገኙ ነፍጓል፤ ተብሏል። ይህም ጉግል፣ ያለተፎካካሪ በማስታወቂያ በሚያገኘው ገቢ አማካይነት፣ ከዓለም ሀብታም ኩባንያዎች አንዱ እንዳደረገው፣ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG