የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፐሎሲ የቻይናን ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት ከጥቂት ሰዓታት በፊት ታይፔይ - ታይዋን ገብተዋል። የፐሎሲ ታይዋንን የመጎብኝት ጭምጭምታ ከተሰማ አንስቶ አሜሪካና ታይዋን ‘የግዛቴ አካል ነች’ የምትለው ቻይና ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ከርመዋል።
ፐሎሲ ታይዋን ከገቡ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድ ስትዝት ቤጂንግ ስትዝት ሰንብታለች። ፐሎሲ አምስት የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት እንደራሴዎች ያሉበትን ቡድን መርተው አመሻሹ ላይ ታይዋን ገብተዋል።
“የአሜሪካ ኮንግረስ ቡድን ታይዋንን መጎብኘቱ አሜሪካ ለታይዋን ንቁ ዴሞክራሲ ያላትን የማይናወጥ ድጋፍ ያሳያል” ብለዋል ፐሎሲ ታይፔይ እንደደረሱ። ፐሎሲ ታይዋን ከመድረሳቸው ቀደም ብሎ በርካታ የቻይና ተዋጊ ጄቶች በታይዋን የባህር ወሽመጥ አቅራቢያ ሲያንዣብቡ እንደነበር ሮይተርስ በስም ያልተጠራ ምንጩን ጠቅሶ ዘግቧል።
አውሮፕላኖቹ “በጣም ተንኳሽ” የሆነና በጥቂቱም ሁለቱን ወገኖች የሚለየውን አካባቢ “ነክተው” መመለሳቸውን ምንጩ ተናግሯል። አፈጉባዔ ፐሎሲና ቡድናቸው ማሌዢያንና ሲንጋፖርንም ጎብኝተዋል።
የጉብኝታቸው ዓላማ ለአካባቢው ሃገሮች የአሜሪካን የማይናወጥ ድጋፍ ለማረጋገጥ እንደሆነ ፐሎሲ ከትናንት በስተያ ዕሁድ ተናግረዋል።