በአሜሪካ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የእግር ኳስ የፍጻሜ ጨዋታ ትናንት እሁድ ተካሂዷል።
በፍፃሜው ጨዋታ የካንሳስ ሲቲው ቺፍስ፣ የሳን ፍራንሲስኮ ፎርቲ ናይነርስን ተጨማሪው ሰዓት ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰከንዶች ሲቀሩት ባስቆጠረው ነጥብ፣ 25 ለ22 በሆነ ውጤት አሸንፎ ዋንጫውን አንስቷል።
ካንሳስ ሲቲ ቺፍስ፣ ሻምፒዮንነቱን በተከታታይ ለሁለት ዓመታት ሲወስድ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ደግሞ ለሶስተኛ ግዜ አሸናፊ መሆኑ ነው። ‘ሱፐር ቦውል’ ብለው የሚጠሩትን የፍጻሜ ጨዋታ አንድ ቡድን በተከታታይ ዓመታት ሲያሸንፍ፣ ከሃያ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ መሆኑ ነው።
በጨዋታው አሸናፊውን ነጥብ ያስቆጠረው መኮል ሃርድማን፣ ግቡን ካስቆጠረ በኋላ ለደቂቃዎች የት እንዳለ እንደማያውቅ፣ በኋላ ግን የቡድኑ ዓምበል ፓትሪክ ማሆምስ ወደ እርሱ ተጠግቶ እንዳሸነፉ ሲነግረው ከነበረበት ሁኔታ ውስጥ እንደነቃ ለጋዜጠኞች ተናግሯል። አምበሉ ፓትሪክ ማሆምስ የኮከብ ተጨዋችነቱን ሽልማት አግኝቷል።
ጨዋታው፣ ‘ሲን ሲቲ’ (‘የኃጢአት ከተማ’) ተብላ በምትጠራው ላስ ቬጋስ፣ አሊጃንት ስቴዲየም ሲካሄድ፣ በሥፍራው 65 ሺሕ የኳስ አፍቃሪዎች ሲታደሙ፣ በቴሌቭዥን መስኮት ደግሞ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል።
ከኳስ ውድድርነቱ ባለፈ፣ ለአገሬው ሰዎች እንደ አንድ ከፍተኛ የዓመቱ ክንዋኔና ዓውደ ዓመት የሚቆጠረው የፍጻሜው ቀን፣ ከፍተኛ የቴሌቭዥን ተመልካቾች ቁጥር የሚመዘገብበትም ቀን ነው። ለዚህም ይመስላል በቴሌቭዥን ለሚቀርቡት ማስታወቂያዎች እና በዕረፍት ሰዓት ለሚቀርበው የሙዚቃ ትዕይንት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። ኩባንያዎች ማስታወቂያውን ለማሠራት እና ለተዋንያኖች ከሚከፍሉት በተጨማሪ፣ ለ30 ሰከንድ ማስታወቂያ የአየር ሰዓት 7 ሚሊዮን ዶላር እንደከፈሉ ተዘግቧል።
ትናንት ከቀረቡት ማስታወቂያዎች ውስጥ ተዋንያን ቤን አፍሌክ፣ ማት ዴመን እና ጀኒፈር ሎፔዝ በጋራ የሠሩት የደንኪን ዶናት የአንድ ደቂቃ ማስታወቂያ፣ በአስቂኝነቱ ተመዝግቧል። በአንድ ወቅት የትዳር አጋር የሆኑት ቤን አፍሊክ እና ጀኒፈር ሎፔዝ፣ በሆሊውድ ያዝ ለቀቅ በሚያደርገው የፍቅር ግንኝነታቸው መታወቃቸውና፣ ማስታወቂያው ሎፔዝ በሥራ ላይ እያለች አፍሌክ ጓደኞቹን ሰብስቦ ድንገት መምጣቱን በማሳየቱ ተመልካቹን ፈገግ አሰኝቷል።
አጎታቸው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የሆኑት፣ የሮበርት ኬኔዲ ጁኒየር የምርጫ ማስታወቂያ ግን፣ በቤተሰባቸው አባላት ጭምር ውግዘት እንዳስከተለ ተነግሯል። ኬኔዲ ጁኒየር በአሜሪካ ፖለቲካ ትልቅ ስም እና ዝና ካላቸው አጎታቸው ጆን ኤፍ ኬኔዲ ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳላቸው አድርገው መቅረባቸው ለቅሬታው ምክንያት ሳይሆን አልቀረም።
በቴሌቭዥን በቀጥታ በሚተላለፈው ጨዋታም ሆነ በስቴዲየሙ ታዳሚ ዘንድ የነበረው ሌላው ትኩረት፣ በዕረፍት ሰዓት የሚቀርበው የሙዚቃ ትይንት ነው። የሪትም ኤንድ ብሉስ አቀንቃኙና ዘፈኑን ከዳንሱ ችሎታው ጋር በአንድ ላይ በመድረክ የሚያስኬደው አሸር፣ በአሊሺያ ኪስ፣ ሉዳክሪስ እና ሌሎችም አቀንቃኞች ታጅቦ ያቀረበው ትርዒት፣ ታዳሚውን እና የቴሌቭዥን ተመልካቹን ቁጭ ብድግ አሰኝቷል።
ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፈው፣ የታዋቂዋ አቀንቃኝ ቴይለር ስዊፍት ጉዳይ ነው። የካንሳስ ሲቲ ቺፍስ ኮከብ ተጨዋቾች ከሆኑት አንዱ የሆነው ትራቪስ ኬልስ ፍቅረኛ የሆነችው ቴይለር ስዊፍት፣ የቴሌቭዥን ካሜራውን እና የስቴዲየም ታዳሚውን ዓይን በተደጋጋሚ ስትስብ ተስተውላለች፡፡ ቴይለር ስዊፍት ከትራቪስ ጋር የፍቅር ግንኙነት ከጀመሩ ወዲህ፣ በየጨዋታው እየተገኘች ድጋፍ በመስጠቷ፣ የስቴዲየም ትኬት ሽያጩንም ሆነ የእግር ኳሱ ሊግ ለገበያ የሚያቀርበው አልባሳትና ሌሎችም ሸቀጦች ሽያጭ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች እንዲጨምር ማድረጉ ሲዘገብ ቆይቷል። እግር ኳሱ አዲስ ተመልካቾችን እንዲስብ ማድረጓም ተነግሮላታል።
ትራቪስ በዕለቱ ነጥብ ለማስቆጠር ባይችልም፣ ከፍጻሜው በኋላ ወደ ሜዳው ከወረደችው ቴይለር ጋር በመተቃቀፍና በመሳሳም ደስታውቸን ሲገልጹ፣ ማሕበራዊ ሚዲያው ወዲያውኑ በፎቷቸው ተጥለቅልቋል።
ትራቪስ በጨዋታው የመጀመሪያ ሩብ ላይ ለጊዜው ተቀይሮ እንዲወጣ በማድረጋቸው፣ አሰልጣኙን አንዲ ሪድን በብስጭት ሲገፈትር፣ በዕድሜ ገፋ ያሉት ሪድ ላለመውደቅ ሲንገዳገዱ ተስተውለዋል። አሰለጣኙ ቂም አልያዙም። ስለጉዳዩ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸውን ጥያቄ፣ በሳቅ አልፈውታል።
በአሜሪካ የእግር ኳስ ፍፃሜው፣ ልክ እንደሌሎቹ አውደ ዓመቶች፣ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ በአንድ ቦታ ሰብሰብ ብሎ በጋራ ቀኑን የሚያሳልፍበት፣ ምግብ መጠጡ ቀድሞ የሚዘጋጅበት ቀን ነው። የኳሱም ሆነ ከኳሱ ጋር ተያይዘው የተከሰቱት ነገሮች ለሳምንታት የወሬ ርዕስ ሆነው ይቀጥላሉ።
መድረክ / ፎረም