ጀኒቫ ላይ ሊካሄድ በታቀደው የሰላም ንግግር ላይ የሱዳን ሠራዊት ተወካዮች ባይገኙም በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት እንደሚቀጥል አሜሪካ አስታውቃለች፡፡
በሱዳን የሚታየውን ቀውስ ለማስቆም አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ጥረት ለመጀመር ለንግግሩ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጀኒቫ መግባታቸውን በሱዳን የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ፔሪዬሎ አስታውቀዋል።
በሱዳን መንግስትና በአሜሪካ መካከል ትላንት እሁድ ጀዳ ላይ ሲደረግ የነበረው ምክክር ካለስምምነት በመጠናቀቁ፣ የሱዳም መንግስት ወይም ሠራዊት በጀኒቫው ንግግር ላይ ይገኝ እንደሁ ማረጋገጫ አልተሰጠም። ይህም ረቡዕ ይጀመራል የተባለው የተኩስ አቁም ድርድር ላይ ጥላ አጥልቷል።
አሜሪካ ለሁለቱም የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ግብዣውን ብትልክም፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በድርድሩ እንደሚገኝ ወዲያውኑ ሲያስታውቅ፣ በጀኔራል አበደል ፋታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ሠራዊት በውይይቱ ላይ ይገኝ እንደሁ እስከ አሁን አላስታወቀም። ከሱዳን ሰራዊት ጋራ የሚደረገው ምክክር እንደሚቀጥል የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ትላንት እሁድ ለቪኦኤ ተናግረዋል።
በሱዳን ለሚታየው ቀውስ ወታደራዊ መፍትሄ እንደማይኖር የአሜሪካ ባልሥልጣናት በመናገር ላይ ናቸው።
መድረክ / ፎረም