የአሜሪካ መንግስት ከሰሃራ በታች ላሉ ሃገራት ለተጨማሪ የሰብዓዊ ሥራ የሚውል 536 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ዛሬ አስታውቋል፡፡
ከተጠቀሰው ገንዘብ ውስጥ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የሰብዓዊ አጋሮች 97 ሚሊዮን ዶላር መመደቡንና ከዚህም ውስጥ 87 ሚሊዮን ዶላሩ ለስደተኞች የሚውል መሆኑን በአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የሰብዓዊ ደህንነት፣ ዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ረዳት ፀሃፊ የሆኑት ኡዝራ ዜያ ዛሬ አዲስ አበባ ላይ አስታውቀዋል።
ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት 38 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያቸው እንደተፈናቀሉ ያወሱት ረዳት ፀሃፊዋ፣ ከዚህ ውስጥ 30 ሚሊዮን የሚሆኑት የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሲሆኑ፣ ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ የሃገራቸውን ድንበር ተሻግረው የተሰደዱ ናቸው።
“የለጋስነት ምልክት” ብለው ረዳት ፀሃፊዋ የገለጿት ኢትዮጵያም 1.8 ሚሊዮን ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ መሆኗን አመልክተዋል።
አሜሪካ በዓለምም ሆነ በአፍሪካ ትልቋ የሰብዓዊ ርዳታ ለጋሽ መሆኗን የጠቀሱት ኡዝራ ዜያ፣ በሱዳን ጦርነት ለተፈናቀሉ 1 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በዚህ ዓመት ብቻ ከሰሃራ በታች ላሉ ሃገራት 3.7 ቢሊዮን ዶላር መለገሷን አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም