የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መቆጣጠር እና መከላከል ማዕከል /ሲዲሲ/ የሃምሳዎቹም ክፍለ ግዛቶችና የበርካታ ትላልቅ ከተሞች የጤና ባለሥልጣናት እኤአ ከህዳር 1 ፕሬዚደንታዊ ምርጫው ከሚካሄድበት ዕለት ከሁለት ቀን በፊት የኮሮናቫይረስ ክትባት ለማከፋፈል ዝግጅት እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ መላኩን አረጋገጠ።
ሲዲሲ ባለ አራት ገጽ ማሳሰቢያውን ባለፈው ሳምንት ሃሙስ መላኩን እና እስከ ጥቅምት 1 ባለው ጊዜ ዕቅዳቸውን እንዲያጠናቅቁ ማሳሰቡን ትናንት በቀዳሚነት ዘ ሜክላቺ የተባለው የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ኒውዮርክ ታይምስ በዘገባው የሲዲሲ ዳይሬክተር ሮበርት ሬድፊልድ ኒውዮርክ፣ ቺካጎ፣ ፊላዴልፊ፣ ሂዩስተን እና ሳን አንቶንዮ ከተሞችን ጨምሮ ለለሀገሪቱ ክፍለ ግዛቶች በሙሉ ማሳሰቢያውን እንደላኩ አመልክቷል።
ሲዲስ የላከው ማሳሰቢያ ወቅት የብሄራዊ የተላላፊ በሽታዎች ኢንስቲቱዩት ዋና ድሬክተር አንተኒ ፋውቺ ይህ እአአ 2020 ሳያበቃ የጤና አደጋ የማያስከትል እና የሚሰራ ክትባት ይገኛል ብለው እንደሚተማመኑ ከተናገሩበት ቃለ መጠይቃቸው ጋር ተገጣጥሟል።
ዶክተር አንተኒ ፋውቺ ያን ቢሉም እንዲሆን የማንፈልገው ነገር ክትባት በሚገባ መስራቱን የሚያሳይ ፍንጭ ሳይገኝ በጥድፊያ ሥራ ላይ እንዲውል መፍቀድን ነው ብለዋል።
ሌሎች ኤክስፐርቶችም የክትባት የሰው ላይ ሙከራዎች ሳይጠናቀቁ ሥራ ላይ እንዲውሉ ፈቃድ መስጠት አንድም ለጤና አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል ክትባትን የሚቃወሙ ወገኖች አመለካከት ይብሱን ሊያጠናክር ይችላል በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።