ዓመታዊው የዩናይትድ ስቴትስ የአገሮች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግምገማ ሪፖርት ይፋ ሆነ።
በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌና በሌሎች ዓለም አቀፍ ሥምምነቶች የታቀፉ የግለሰቦች የሲቪል፥ የፖለቲካ፥ የሥራና አጠቃላይ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ መረጋገጥ የሚከታተለው ዓመታዊ ዘገባ ዘንድሮም ቁጥራቸው ሁለት መቶ የሚደርስ አገሮችን የዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ መርምሯል።
የፖለቲካ አመለካከትን መሠረት ያደረገ፥ ከሕግ ውጭና በዘፈቀደ የሚፈጸም እሥር፤ የገቡበት ያለመታወቅ ወይም ደብዛ መጥፋት፤ ለእንግልትና የጭካኔ ምግባር መጋለጥ፤ እንዲሁም የንግግርና የፕሬስ ነጻነት አፈናን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች መገፈፍ ሪፖርቱ ትኩረት ካፈረገባቸው አበይት ጉዳዮች ውስጥ ናቸው።
“ለግለሰብ ማንነት ክብርና ከሕግ ውጭ ከሚፈጸሙ ማናቸውም ጥቃቶችና የመብቶች ገፈፋ መጠበቃቸውን ማረጋገጥ” ሲል ይንደረደራል፤ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ይፋ የተደረገው አርባ አንደኛው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአገሮች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግምገማ ዓመታዊ ሪፖርት።
በሰባት ዋና ዋና ክፍሎችና ከሰላሳ በላይ በሚሆኑ ንዑስ ርዕሶች ሥር የሰፈረው ዓመታዊ ዘገባ:- “በዘፈቀደ የመኖር መብትን መቀማትና በፖለቲካ ሳቢያ የተውጠነጠኑ ግድያዎች፤ የገቡበት ያለመታወቅ፤ ስቃይና እንግልት፤ ሰብዓዊነት የጎደለው የጭካኔ ተግባር፣ እስርና የመሳሰሉትን በመንግስት ኃይሎች የተፈጸሙ የበዙ ጥቃቶች ይዘረዝራል። የንግግርና የፕሬስ ነጻነት አፈናና ሌሎች አንድ ዜጋ ሰው በመሆኑ ሊኖረው የሚገቡ መብቶች መገፈፍም ይመለከታል።
ሪፖርቱ እነኚሁኑ ጭብጦች ተንተርሶ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባወጣው “በመንግስት ኃይሎች ተፈጸሙ” ያላቸውን ቁጥራቸው የበዛ እርምጃዎች ዘርዝሯል።
ባለፈው የአውሮፓውያኑ 2016ዓም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተቃውሞ የወጡ በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የዘገበው ሪፖርት አክሎም፣ መንግስት ያቋቋመው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮምሽን በሰኔ ወር ለአገሪቱ ፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት 28 የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል 173 ሰዎች መገደላቸውን ያመለከተበትን ጠቅሷል። ገለልተኛው የሰብዓዊ መብት ጉባኤ - ሰመጉ በበኩሉ ባለፈው ዓመት በመጋቢት ወር ባወጣው ዘገባ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2015 ዓም ከሕዳር እስከ የካቲት ባለው ጊዜ በ33 ወረዳዎች ባካሄደው ጥናት ከመቶ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ማረጋገጡን ሪፖርቱ አመልክቷል።
መንግስታዊው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮምሽን በአማራ ክልል በተለይ በቅማንት “የመንግስት የጸጥታ ሠራተኞች ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅመዋል” ማለቱንና ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች HRW’ም ባለፈው ነሃሴ ወር ባወጣው ዘገባ በአካባቢው በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ5 መቶ በላይ ናቸው፤ ያለውን ጠቅሶ ዓመታዊው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግምገማ ሪፖርት አትቷል።
የነሃሴውን የቂሊንጦ የፌድራል እስር ቤት ቃጠሎ ተከትሎ በርካታ ታሳሪዎች ጠያቂ በሚያያቸው ሁኔታ ገደብ መጣሉን የሕግ አማካሪ ጠበቆቻቸውን ዋቢ ያደረገው የዩናይትድ ስቴትስ ዓመታዊ የአገሮች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዘገባ ጽፏል። የፖለቲካ እስረኞች የሕክምና አገልግሎት አያገኙም፤ ካገኙም ከመደበኛው የተለየ መሆኑን የሚጠቁሙ ቅሬታዎች በተደጋጋሚ መቅረባቸውን ሪፖርቱ ዘርዝሯል።
የፕሬስና የንግግር ነጻነት ገደቦች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ይበልጥ መራቆታቸውን የዘረዘረው ዓመታዊው ሪፖርት የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቭዥን ኢሳት እና የኦሮሞ መገናኛ ብዙኃን እንዳይታዩ መደረጋቸውንም ጥናቱ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ መንግስት በጥቅምት ወር መጀመሪያ በተንቀሳቃሽ ስልኮች አማካኝነት የሚሰራጨውን የኢንተርኔት አገልግሎት በአዲስ አበባ፥ በአብዛኛው ኦሮሚያ እና ሌሎች አካባቢዎች ሙሉ ሙሉ መቋረጡን፤ ፌስ ቡክ’ን፣ ትዊተር’ን ኢንስታግራም’ን ዩ-ቲዩብ’ን ስካይፕ’ን ዋትሳፕ’ን ቫይበር’ን ጨምሮ አብዛኛውን የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ገጾች ማግኘት እንዳይቻል ማድረጉን አመልክቷል።
የዋሽንግተን ፖስት፥ የኒው ዮርክ ታይምስ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን፤ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎችእና አማዞንን የመሳሰሉ የኢንተርኔት መደብሮችን ማግኘት የማይቻሉ መሆናቸው ተጽፏል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1961 ዓም የጸደቀውን “የውጭ እርዳታ አንቀጽ” በመባል የሚታወቀውን እና ሌላውን እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1974 ዓም የወጣውን “የንግድ ድንጋጌ” የተባለ አንቀጽ መሠረት ያደረገው አርባ አንደኛውን የአገሮች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግምገማ ሪፖርቱን ለዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ልኳል።
“የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃና ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲረጋገጥ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ፖሊሲ አብይ አካል መሆኑን ጠቁመው የተረጋጋ፥ ደህንነቱ የተረጋገጠ እና ሕልውናው ለተረጋገጠ ማኅበረሰብ መሠረት ነው፤” የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር Rex W. Tillerson ዘገባው ቁጥራቸው ሁለት መቶ የሚደርስ የመንግስታቱን ድርጅት አባል አገሮች በሙሉ እና ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ እርዳታ የሚያገኙ አገሮችን ያካተተ መሆኑን ለሪፖርቱ በጻፉት መግቢያ ገልጸዋል።
ስድስት የፌድራልና አንድ መቶ የክልል እስር ቤቶች ኢትዮጵያ በእስር ቤቶቿ ያስገባቻቸውን ዜጎች ቁጥርና የፍትህ ሂደት፤ እንዲሁም ሌሎች “የመብት ነጠቃ” በሚል ያሠፈራቸውን ዝርዝሮች ዓመታዊው ዘገባ ተችቷል። አድማጮች የሪፖርቱን ሌሎች ዝርዝሮችና እንዲሁም የኤርትራን የሰብዓዊ መብት አያያዝ የተመለከተውን ጨምረን በቀጣይ ፕሮግራማችን ለመዳሰስ እንሞክራለን።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ