ዋሺንግተን ዲሲ —
የዩናይትድ ስቴትስ የኤሮኖቲክስና የጠፈር አስተዳደር - ናሳ የጠፈር ምልልሱን ሥራ ለግል ኩባንያዎች ኮንትራት እየሰጠ ነው፡፡
ከእነዚህ የግል ኩባንያዎች አንዱ ዋና መሥሪያ ቤቱ ቨርጂንያ የሆነው ኦርቢታል ሳይንስስ ኮርፐሬሽን በሚያንቀሳቅሰው የ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ኮንትራት ኅዋ ውስጥ ለሚገኘው ዓለምአቀፍ ጣቢያ ስንቅና ቁሳቁስ እየላከ ይገኛል፡፡
ከእነዚህ ተልዕኮዎች አንዱ ከትናንት በስተያ ተስተጓጉሏል፡፡
በአንታርስ ሮኬት ከቨርጂንያው ማስወንጨፊያ ከሁለት ቶን በላይ ውኃ፣ ምግብና የምርምር ቁሣቁስ ይዛ የተነሣችው መንኩራኩር ከተተኮሰች ከጥቂት ሰከንዶች በኋላ ፈንድታለች፡፡
በሰው ላይ ምንም ጉዳት አይድረስ እንጂ መላው ጭነት በፍንዳታውና በእሳቱ ወድሟል፡፡
የማስወንጨፊያው ማማ ብዙ ጉዳት ደርሶበታል፡፡
በናሳ የጎዳርድ የጠፈር በረራ ማዕከሉ የፕላኔታሪ ሳይንስ መምሪያ ረዳት ኃላፊ ዶ/ር ብሩክ ላቀው ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ ጉዳቱ እስከ 200 ሚሊየን ዶላር እንደሚገመት ጠቁመው የአደጋው መንስዔና አጠቃላዩ የጉዳት መጠን ግን እየተጠኑ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡