ዩናይትድ ስቴትስ ለደቡብ ኮርያ የሚሣይል ጥቃት ከለላ ሥርዓት ለመገንባት ሶል አንድ ቢሊዮን ዶላር እንድትከፍል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ያቀረቡትን ሃሣብ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ፈጥኖ ተቃወመ፡፡
ከሰሜን ኮርያ ሊጣል ከሚችል ጥቃት ደቡብ ኮርያን ለመከላከል አሜሪካ የመከላከያ ሥርዓቱን በመዘርጋቷ ጉዳይ ላይ በተደረሰው ስምምነት ውስጥ የተለወጠ ቃል አለመኖሩን፤ እንዲሁም የተከላ፣ የእንቅስቃሴና የጥገና ወጭዎችንም ዩናይትድ ስቴትስ እንደምትሸፍን የደቡብ ኮርያ የመከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ታድ በሚል ምኅፃር የሚጠራውን የሚሣይል ከለላ ሥርዓት ለመዘርጋት ስምምነቱ የተደረሰው በቀድሞዎቹ የዩናይትድ ስቴትስና የኮሪያ ፕሬዚዳንቶች ባራክ ኦባማና ፓርክ ጌዩን ሃይ መካከል ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ዛሬ ከሮይተርስ የዜና አውታር ጋር ቃለ-ምልልስ ባደረጉበት ወቅት ግን ኮርያ የከለላ ሥርዓቱ እንዲዘረጋላት ክፍያውን እንድትፈፅም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
አጠቃላዩ ወጭ ወደ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ሊሆን እንደሚችጽል አንድ የአሜሪካ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን አመልክተዋል፡፡
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ