በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአሜሪካን የደቡብ ኮርያ የንግድ ውዝግብ


ፎቶ ፋይል - ቡሳን፣ ደቡብ ኮሪያ
ፎቶ ፋይል - ቡሳን፣ ደቡብ ኮሪያ

ደቡብ ኮሪያ “በኤሌክትሪክ መኪና ምርቶቼ ላይ አግላይ የሆነ ድርጊት በዩናይትድ ስቴትስ ተፈጽሞብኛል” ማለቷ ዋሽንግተን የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ግሽበት ለማሻሻልና እሲያን በተመለከተ ያላትን ሰፊ የኢኮኖሚ ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ ከሸሪኮቿ ጭምር የገጠማትን ፈተና ያሳያል ሲል የቪኦኤው ዊሊያም ጋሎ ከሶል ደቡብ ኮሪያ ዘግቧል።

ባለፈው ወር በአሜሪካ የጸደቀውና የኢኮኖሚ ግሽበትን ለመቋቋም የወጣው ህግ በሃገሪቱ የተመረቱ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ለሚገዙ አሜሪካውያን እስከ 7ሺ 500 ዶላር የታክስ ቅናሽ እንደሚያደርግ መደንገጉና፣ ከውጪ ለሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖች ሲሰጥ የነበረውን የታክስ ቅናሽ ማስወገዱ፣ እንደ ቻይናና ደቡብ ኮሪያ ያሉ ለአሜሪካ ገበያ የሚያቀርቡ አምራቾችን ችግር ውስጥ ከቷቸዋል።

ከተስላ ቀጥሎ በአሜሪካ ከፍተኛ ሽያጭ የሚያከናውኑት የደቡብ ኮሪያው ኽንዴይ እና ሸሪኩ ኪያ በአዲሱ ህግ ትልቅ ተጎጂዎች መሆናቸው ታውቋል።

የደቡብ ኮሪያ የንግድ ባለሥልጣናትና የፖለቲካ ሰዎች በአሜሪካ በውጣው ህግ ላይ ቁጣቸውን ወዲያው አሰምተዋል። የዓለም ንግድ ድርጅት መርህዎችን የሚጥስና፣ በዩናይትድ ስቴትስና ደቡብ ኮሪያ መካከል የተደረሰውን ነጻ ንግድ ስምምነት የሚጻረር ነው ሲሉ አማረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሃገሪቱ የመኪና አምራቾች መዲና ተብላ በምትጠራው ዲትሮይት ከተማ፣ ሃገሪቱ ወደ ኤሌክትሪክ መኪና የምታደርገውን ሽግግር ለማስተዋወቅ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው።

ባይደን በታላቁ “የዲትሮይት የመኪናት ዕይንት” ላይ በመገኘት የኢኮኖሚ ግሽበትን ለመቋቋም የወጣው ህግን ለማስተዋወቅና፣ አንዱ ጠቀሜታውም በሃገሪቱ የተመረቱ የኤሌክትሪክ መኪናዎችን ለሚገዙ አሜሪካውያን እስከ 7ሺ 500 ዶላር የታክስ ቅናሽ የሚሰጥ መሆኑን በተመለከተ ንግግር አድርገዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ዋና ዋናዎቹ መኪና አምራቾች የኤሌክትሪክ መኪና እንዲሁም ለመኪናው የሚያስፈልገውን ባትሪ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን በአሜሪካና ካናዳ ለመግንባት ዕቅድ መያዛቸውን አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG