ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ እና ቀዳማዊት ዕመቤት ሚላኒያ ትረምፕ በጥቃቱ ዕለት በሽብርተኞች ከጠለፉት ሁለት አውሮፕላኖች እንደኛው ከኒውዮርክ የዓለም የንግድ ማዕከል ህንፃ ጋር ባጋጩበት ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከአርባ ስድስት ደቂቃ ላይ ዋይት ኃውስ ቤተ መንግሥት ደጃፍ ላይ በተከናወነ የህሊና ፀሎት ተካፍለዋል።
ከዚያም ፕሬዚዳንቱ በዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ፔንታጎን በተከናወነ ሥነ ስርዓት ላይ የአልቃይዳ ሽብርተኞች የጠለፉትን አውሮፕላን ከህንፃው ባጋጩበት ጥቃት ለተገደሉት 184 ሰዎች ቤተሰቦች ንግግር አድርገዋል።
በኒው ዮርክ ግራውንድ ዜሮ ተብሎ በሚጠራው እና በመስከረም አንዱ ጥቃቶች በወደሙት የዓለም የንግድ ማዕከል ህንፃዎች በነበሩት ስፍራ ላይ በሚገኘው መታሰቢያ ላይ በየዓመቱ በየዓመቱ በሚካሄደው የመታሰቢያ ሥነ ስርዓት ሰለባ የሆኑት ሰዎች ስም ዝርዝር ተነቧል።
የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ ደግሞ ፔንሲልቬንያ ሻንክስቪል ከተማ ላይ በተካሄዱ የመታሰቢያ ሥነ ስርዓቶች ተካፍለዋል። በመስከረም አንዱ ጥቃት የተካፈሉት ሽብርተኞች የጠለፉትን የዩናይትድ እየር መንገድ ከዋይት ኃውስ ጋር ለማጋጨት ይዘው ሲበሩ፣ ተሳፋሪዎች ታግለዋቸው አውሮፕላኑ ሻንክስቪል አቅራቢያ መውደቁ ይታወሳል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ