ዋሺንግተን ዲሲ —
የዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛው ምክር ቤት ትናንት ሀሙስ ምሽቱን የመንግሥትን የመበደር ሥልጣን እስከ ታህሳስ ወር መጀመሪያ ድረስ አራዝሟል፡፡ ይህን በማድረጉም በአገሪቱ ታሪክ በእዳ አከፋፈል ጉድለት ምክንያት ለመጀመሪያ ጊዜ ሊደርስ የነበረውን ቀውስ ማዳኑ ተገልጿል፡፡
የህግ መወሰኛው ምክር ቤት መሪ ቻክ ሹመር ከሪፖብሊካኑ መሪ ሚች መካኔል ጋር ከተደራደሩ በኋላ በምክር ቤቱ መድረክ የተደረሰበትን ስምምነት ይፋ አድርገዋል፡፡
ለዴሞክራቶቹ ያቀረቡት አማራጭ በአገሪቱ ለረጀም ጊዜ በተጠራቀመው የ28.4 ትሪሊዮን ዶላር እዳ ላይ መንግሥት እስከ ታህሳስ ድረስ ወጭውን የሚሸፍንበት 480 ቢሊዮን ዶላር ብድር ብቻ እንዲፈቀድ የሚል ነበር፡፡
ሪፖብሊካኖቹ ህግ አውጭዎች ፕሬዚዳንት ባይደን የጠየቁት፣ የ 2 ትሪሊዮን ዶላር የወጭ በጀት በመፍቀድ የአገሪቱን የእዳ መጠን ከፍ ለማድረግ እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል፡፡
በመወሰኛው ምክር ቤት የጸደቀው ረቂቅ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራ ሲሆን እዚያ ከጸደቀ በኋላ ለፊርማ ወደ ፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት የሚላክ መሆኑን ተገልጿል፡፡