በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሴኔቱ ለዩክሬንና እስራኤል የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጥ ተለዋጭ ረቂቅ ሕግ አቀረበ


የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ (ካፒቶል)
የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ (ካፒቶል)

ለዩክሬን፣ እስራኤል እንዲሁም የድንበርን ደህንነትን ለማስጠበቅ በሚል 118 ቢሊዮን ዶላር ሊመድብ ያቀደው ረቂቅ ሕግ፤ በሕግ መወሰኛው ም/ቤት የሪፐብሊካን ዓባላት እንዳያልፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ለዩክሬን እና ለእስራኤል ርዳታ ለመስጠት ያቀደ ሌላ የ95 ቢሊዮን ዶላር ረቂቅ ለማቅረብ ም/ቤቱ በዝግጅት ላይ ነው።

ከዚህ ውስጥ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ላላችው ዩክሬን ስድሳ ቢሊዮን፣ እንዲሁም ከሃማስ ጋር ጦርነት ውስጥ ላለችው እስራኤል ደግሞ 14 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት መታቀዱ ታውቋል።

“ትረምፕ ከሳምንት በፊት ጣልቃ ገብተው፣ የፖለቲካ ጉዳይ እንዲሆን እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል። በድንበር ላይ ቀውስ ቢፈጠር እንደሚመርጡ ተናግረዋል። ምክንያቱም፣ ለምርጫው ይጠቅመኛል ብለው ስለሚያስቡ ነው። ሌላ የተለየ አማራጭ እንደሚያስፈልገን አውቀን ነበር” ሲሉ የሕግ መውሰኛውን ም/ቤት የተቆጣጠረው የዲሞክራቲክ ፓርቲው መሪ ቸክ ሹመር፣ ድንበርን የሚመለከተውን የረቂቁን ክፍል አስቀርተው፣ ሌላ ረቂቅ ያቀረቡበትን ምክንያት አስረድተዋል።

በሁለቱም ፓርቲዎች በጋራ የተዘጋጀው እና ትናንት እክል የገጠመው ረቂቅ፣ የፍልሰተኞችን ግዚያዊ ማቆያ ማዕከላት ለመጨመር፣ የጥገኝነት ጥያቄያቸው መልስ እስከሚያገኝ በአሜሪካ የሚቆዩበትን አሰራር ለማስቀረት፣ እንዲሁም ድንበሩን የሚሻገሩ የፍልሰተኞች ቁጥር ከተወሰነ በላይ ሲሆን፣ ፕሬዝደንቱ ድንበሩን እንዲዘጉ ስልጣን የሚሰጥ ነበር።

በርካታ የሪፐብሊካን የህግ መወሰኛ ም/ቤት ዓባላት፣ በድርድሩ ወቅት ተሳታፊ እንዳለተደረጉና የድንበር ደህንነትን በተመለከተ ያላቸውን ስጋት ረቂቅ ሕጉ በተገቢው መልስ እንዳልሰጠ በመናገር ላይ ናቸው።

“ረቂቅ ሕጉን ባቀረብን በ24 ሰዓት ውስጥ፣ የሪፐብሊካን ጓዶቼ ሃሳባቸውን ቀየሩ። ማውራት እንጂ፣ በተግባር ማሳየት እንደማይፈልጉ ታወቀ። እናም የድንበር ደህንነት ጉዳይ ለእነርሱ የብሔራዊ ፀጥታ ጉዳይ እንዳልሆነ ታወቀ። ለምርጫ ዘመቻ ጠቀሜታ ሲሉ የተናገሩት ነበር” ሲሉ በግል የሕግ መወሰኛ ም/ቤት አባል የሆኑት ሴናተር ኪርስተን ሲነማ፣ ለረቂቁ አለማለፍ ሪፐብሊካኑን ተጠያቂ አድርገዋል። ዲሞክራቶቹ በበኩላቸው ለዩክሬን የሚሰጠውን ርዳታ ማደናቀፍ፣ ብዙ መዘዝ እንዳሚኖረው በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው። በአዲሱ ረቂቅ ላይ ሳምንቱ ከማለቁ በፊት ድምጽ እንደሚሰጥ ታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG