በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለተራቡ ሶማሊያዊያን እርዳታ የሚያደርሱ ተቋማት በአል-ሸባብ የኮቴ ክፍያ ተጠየቁ


ዩናይትድ ስቴይትስ የእርዳታ አቅርቦቱ እንዲሳለጥ የጠበቁ የአሰራር መመሪያዎቿን አላልታለች

በአፍሪካ ቀንድ ባለፉት 60 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ከ11ሚሊየን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ካላገኙ ለሰብዓዊ እልቂት ተጋላጭ በመሆናቸው፤ ዩናይትድ ስቴይትስ የጸረ-ሽብር ህጓ ላይ የነበሩ የእርዳታ አሰጣጥ አሰራሮቿል አላልታለች።

ዩናይትድ ስቴይትስ በሶማሊያ የምትሰጠው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንደ አል-ሸባብ ባሉ አማጺ ቡድኖች እጅ እንዳይገባ በእርዳታ ድርጅቶች ላይ አስቀምጣው የነበረውን የጠበቀ አሰራር እንዳላላች የባራክ ኦባማ አስተዳድር ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው በዩናይትድ ስቴይትስ የደህንነት መረጃ የሚገለጸው አልሸባብ በሚቆጣጠራቸው የሶማሊያ አካባቢዎች የእርዳታ ስርጭት የሚከናወነው ከዚህ ቀደም በጠበቁ የህግ መስፈርቶች ነበር።

በሶማሊያ 3.7 ሚሊዮን ዜጎች በበረታ ረሀብ መውደቃቸውን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴይትስ ይሄንን ህግ አላልታለች።

“60 በመቶ የሚሆኑት በአልሻባብ ቁጥጥር ስር ባለው ግዛት ስር ናቸው። የረድዔት ድርጅቶች በነዚህ አካባቢዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ ህግ የለም ዋናው ነገር በነዚህ አካባቢዎች ምግብ ማድረስ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ ነው። የረድዔት ድርጅቶቹ በጥንቃቄ ገብተው የሰው ህይወት እስካተረፉ ድረስ የሚጠየቁትን የኮቴ ክፍያም ሆነ ክራይ ከፍለው ቢሰሩ ችግር የለውም” ሲሉ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ዲፕሎማት ዶናልድ ያማማቶ ገልጸዋል።

ዶናልድ ያማሞቶ
ዶናልድ ያማሞቶ

ዋና ዋና የሚባሉ የእርዳታ ድርጅቶች የምግብ፤ የውሃና የህክምና አገልግሎቶችን እንዲያቀርቡ ቢጠይቁም፤ አብዛናውን ሶማሊያ የሚቆጣጠሩት የአልሸባብ አማጺያን አሻፈረኝ ማለታቸው አይዘነጋም።

አልሸባብ የሚፈቅድላቸው የእርዳታ ድርጅቶችም ስራቸውን ለማከናውን ለአማጺያኑ ጉቦ ወይንም የኮቴ እንዲከፍሉ እየተጠየቁ ነው። አስቀድማ ዩናይትድ ስቴይትስ ይህንን አትፈቅድም ነበር። በዚህ አይነት እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶች የአሜሪካ መንግስት ድጋፉን ያቆምባቸው ነበር።

በሴኔቱ የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር የዴላዌሩ ሴናተር ክሪስ ኩንስና በሴኔቱ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ጆኒ አይዛክሰን በተገኙበት የምስክርነት ሰሚ ሸንጎ፤ የኦባማ አስተዳድር ከፍተኛ ባለስልጣናትና የርዳታ ሰራተኞች ሁኔታውን ገልጸዋል፣ ምክራቸውን ሰጥተዋል።

ላለፉት 20 ዓመታት የርስበርስ ጦርነት ሲካሄድባት በቆየችው ሶማሊያ፤ ጦርነትና የዝናብ እጥረት በርካታዎችን እያረገፈ እንደሚገኝና የአገሪቱ ግምሽ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልግ ነው የተገለጸው።

የሶማሊያ የዳቦ ቅርጫት በመሆን ብዙ ምርት ያፍሱ የነበሩት የታችኛው ሸበሌና የባኮል አካባቢዎች የረሃብ መቅሰፍት ቢከሰትም እርዳታ ለማቅረብ ግን አስቸጋሪ ሁኔታ እንደገጠማቸው ነው የእርዳታ ሰራተኞቹ የሚናገሩት።

“የጊዜ እጥረትና ወደ ተጎጂዎቹ መድረስ አለመቻል እየተጋፈጥናቸው ያሉ እጅግ ከባድ ፈተናዎች ናቸው” ብለዋል የዩናይትድ ስቴይትስ የእርዳታ ድርጅት USAID የዴሞክራሲ፣ ግጭትና የሰብዓዊ ርዳታ ምክትል ስራ አስኪያጅ ናንሲ ሊንቦርግ።

የዩናይትድ ስቴይትስ መንግስት ለዚህ ቀውስ አዲስ የመደበው ገንዘብ የለም፤ የዩናይትድ ስቴይትስ የስነ-ህዝብና የስደተኞች ምክትል ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩበን ብርጌዲ እንደሚገልጹት።

“የአሜሪካ መንግስት የምስራቅ አፍሪካ መንግስታትና ህዝቦች በድርቅ በተጎዱ ቁጥር በአጋርነት መስራት ከጀመረች ረጅም ጊዜ ሁኗታል። በዚህ የበጀት ዓመት ብቻ ለሰባዊ እርዳታ የሚውል 459 ሚሊዮን ዶላር ለግሳለች። ይህ ገንዘብ ለስደተኞች፣ አካባቢያቸውን ለሚለቁና በመልካመድራዊ ቀውስ ውስጥ ላሉ ድጋፍ ይውላል።”

ባለስልጣናቱ እንዳስረዱት ዩናይትድ ስቴይትስ ለዚህ ድርቅ አስቀድማ ተዘጋጅታለች። የእርዳታ ሰራተኞች ግን፤ ምንም እንኳን ዩናይትድ ስቴይትስ በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ የምግብ እርዳታ አቅራቢ ብትሆንም፤ በቡሽ አስተዳድር ያገኙ ከነበረው ያነሰ ድጋፍ እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

አሜሪካ በበጀት ቅነሳዋን የውጭ እርዳታ ላይ የምትጥል ከሆነ፤ ካለው የድጋፍ አስፈላጊነት ጋር ተዳምሮ ስራቸውን ሊጎዳ እንደሚችል ነው መርሲ ኮር የተባለ የእርዳታ ድርጅት ሰራተኛ ጀረሚ ከናይንዳይክ የገለጹት።

“ከዚህ ቀደም በቡሽ አስተዳድር ከሶስት አመት በፊት ለነበረው አነስተኛ ድርቅ ካገኘንው በግማሽ ያነሰ ነው።”

ጀረሚ ከናንዳይክ
ጀረሚ ከናንዳይክ

ከናይንዳይክ አክለውም የአለም አቀፉ አትኩሮት በሶማሊያ ላይ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያና ኬንያ ከፍተኛ የሆነ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻቸው አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያሻቸውና ሁኔታው እየተባባሰ መሄዱን ይጠቁማሉ።

“እስካሁን አትኩሮታችን የነበረው ወደ ሶማሊያ ቢሆንም በኬንያ፣ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ያለው ሁኔታም በጣም አሳሳቢ ነው።”

መርሲ ኮር ያሰማራቸው አጥኝዎች ሰፋፊ የኢትዮጵያና ኬንያ አካባቢዎችን ክፉኛ እንደተጎዱ መረጃዎች እየሰበሰቡ ነው። የሞቱና ለሞት የሚያጣጥሩ ከብቶች ለአይናቸው እስኪታክታቸው መመልከታቸውን አስታውቀዋል።

“ኑሯቸው ከከብቶቻቸው ጋር የሆኑት አርብቶ አደሮች በቀን አንዴ መመገብ ተስኗቸዋል፤ አንዳንድ ቀበሌዎች ኗሪዎቻቸው ውሃ ፍለጋ ተሰደው፤ ባዷቸውን ቀርተዋል። ሁኔታው እስከ መስከረም ድረስ ተባብሶ እንደሚቀጥል ነው የተረዳንው” ብለዋል ከናይንዳይክ

ሶማሊያ ውስጥ ያሉ ዜጎች ካሉበት እርዳታ ሊደርሳቸው ባለመቻሉ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ መጠለያ ጣቢያዎች ሲጎርፉ ታይተዋል።

በዚህ የሴኔት የምስክር አድማጭ ኮሚቴ ፊት ቀርበው አስተያየታቸውን የሰጡት የፖሲሲ አማካሪ ፒተር ፋም፤ በሶማሊያ አልሸባብ በረሃብ የተጠቁ ዜጎች በስደት ወደ ጎረቤት አገሮች እንዳይንቀሳቀሱ መከልከሉን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅና ረሃብ ተጎጂዎች ቁጥር ከለት ወደለት እየጨመረ ሄዷል። በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያና ጅቡቲ ከ12 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መጎዳታቸውን የእርዳታ ድርጅቶች ይገልጻሉ።

XS
SM
MD
LG