ዋሽንግተን ዲሲ —
በዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት፣ ሩሲያ ዩክሬንን ብትወር፣ በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ “የማዕቀቦች ሁሉ እናት” ብለው የጠሩትን ማእቀብ፣ በሩሲያ ለመጣል መግባባታቸው ተነገረ፡፡
የውጭ ጉዳይ ኮሜቴው ሊቀመንበር ሮበርት መንዴዝ የህግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት ዩክሬን ላይ የሚፈጸም ወረራ ቢኖር በሩሲያ አገዛዝና በሩሲያ ዜጎች ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የፋይናስ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል እምርጃ መውሰድ በሚያስችለው ጥቅል እቅድ ላይ ግራና ቀኝን ያሉት የምክር ቤት አባላት የተስማማ አቋም መያዛቸው ተመልክቷል፡፡
መንዴዝ ባለፈው እሁድ በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ፣ ከፍተኛው ማዕቀብ፣ ወሳኝ ናቸው የተባሉትን የሩሲያ ባንኮችን፣ እንዲሁም የምጣኔ ሀብታቸውን ሊያሸመደምድ የሚችልና፣ በሩሲያ ዜጎች የግልና የጡረታ ሂሳባቸውን የሚያናጋ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡