ሚዝዩሪ ሴንት ሉዊስ በሚገኘው አሜሪካን ዩኒቨርስቲ የተካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሁለተኛ ዙር ክርክር በሞቀ ሁኔታ ተጀምሮ ተጠናቅቋል፡፡
እሰጥ አገባው የተጀመረው የኃይል ቃላትን ጭምር ባዘሉ ንትርኮች ቢሆንም የተጠናቀቀው ግን ሁለቱም አንዱ ስለሌላኛው በተናገሯቸው የመልካም ሰው መገለጫ ቀላት ነበር፡፡
“የእናንተ ምግባር ለዛሬው ወጣት ትውልድ አርዓያ ሊሆን ይችላል ብላችሁ ታስባላችሁ ወይ?” የሚል ጥያቄ ነበር የንትርኩ መክፈቻ፡፡
ትራምፕ ሰሞኑን በወጣባቸው በድብቅ ሲናገሯቸው በነበሩ የብልግና ቃላት የታከሉበት ንግግር በብዙዎች ዘንድ ያስወቀሣቸውና የራሣቸውን የሪፐብሊካን ፓርቲውን መሪዎች፣ እንደራሴዎችና አገረ ገዥዎች ሳይቀር ያስቆጣ ሲሆን ዶናልድ ትራምፕ ስለቃላቱ ይቅርታ ጠይቀው ያልኩትን ግን አላደርግኩም ብለዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ለመቆየት ያልፈለጉት ትራምፕ ወዲያውኑ ከጥያቄው ወጥተው “አይሲስን እደመስሣለሁ፤ ሃገራችንን መልሼ ታላቅ አደርጋለሁ፤” ወደሚሉ ሃሣቦች ገብተዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ቀጥለውም “እኔ ፕሬዚዳንት ሆኜ ከተመረጥኩ የእርስዎን ጉዳይ ብቻ የሚመረምር ልዩ አቃቤ ሕግ አቋቁማለሁ፤ ምክንያቱም የእርስዎን ያህል የዋሸ አላየሁም፡፡ የጠፉ 33 ሺህ ኢሜሎችን ጉዳይ አስመረምራለሁ፡፡ ያኔ ወኅኒ ይወርዳሉ” ብለዋቸዋል፡፡
“ኦባማኬር” በሚል ተቀጥያ ስም የሚታወቀው የተጠቃሚን አቅም ግምት ውስጥ ያስገባ ይሆናል የተባለው የጤና መድኅን ሕግ ለአቅም ተመጣጣኝ አልሆነም፤ ምን ታደርጋላችሁ? ተብለው ሂላሪ ሲመልሱ “እርግጥ ነው ችግር አለበት፤ አስተካክለዋለሁ፤ ሃያ ሚሊየን ሰው እየተጠቀመበት ነው” ብለዋል፡፡ ትራምፕ ደግሞ “ኦባማ ኬር አደጋ ነው፤ ለሰዉም ለሃገራችንም አደጋ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ እሠርዘውና በሌላ እተካዋለሁ” ብለዋል፡፡
“በሙስሊሞች ጉዳይ ላይ ያለዎት አቋም ሃገራችንን የተለየ ገፅታ አያሰጣትም?” የተባሉት ዶናልድ፡- “እንደዚያ ካልሆነ ችግራችን ይቀጥላል” ብለዋል፡፡ ሂላሪ ደግሞ “እንደዚያ ያለ አቋምና አካሄድ ለጠላቶቻችን የመጫወትን ያህል ነው” ብለዋል፡፡
ሂላሪ ዶናልድን ሲከስሱ “ግብር አይከፍሉም፤ የግብር ሠነዶችዎ ሲወጡ ግንኙነቶችዎም ገሃድ ይወጣሉ፡፡ ምናልባት ከሩሲያም ጋር መናገድ ይፈልጉ ይሆናል” ብለዋቸዋል፡፡ ዶናልድ ሲመልሱም “እኔ ፑቲንን አላውቀውም፤ ከሩሲያ ጋር ግን ጥሩ ግንኙነት ቢኖረን ግን አይከፋም” ብለዋል፡፡ ትራምች አክለውም “እኔ ግብር እከፍላለሁ፤ ለመሆኑ ሂላሪ ሴናተር በነበሩ ጊዜ ሕጉን ለምን አልለወጡትም? ምክንያቱም ወዳጆቻቸውም በክፍተቱ ስለሚጠቀሙ ነው” ብለዋል፡፡
ሂላሪ ለዚህ የትራምፕ ክስ በሰጡት ምላሽ “የእኔ ስም ከአራት መቶ ድንጋጌዎች ጋር ተያይዟል፤ መለወጥ ያልቻልኩት ሴናተር የነበርኩት በሪፐብሊካን ፕሬዚዳንት ዘመን ስለነበረ ነው” ብለዋል፡፡
ትራምፕ ስለሶርያና ስለኢራቅ ጦርነት ሲናገሩ “ለጦርነቶቹ መነሣት ክሊንተንን ተጠያቂ አድርገው አሣድ፣ ሩስያና ኢራን አይሲስን እየወጉ ናቸው፡፡ እኛ የት ቦታ እንደምናጠቃ ቀድመን እንናገራለን፡፡ ምን ዓይነት ስቱፒድ ሃገር ነው ያለን? ከመታን በኋላ እኮ መናገር እንችል ነበር” ብለዋል፡፡
ኢነርጂን አስመልክቶ ትራምፕ ሲናገሩ “ኢነርጂአችን በኦባማ አስተዳደር ተጠፍሮ ተይዟል፤ ክሊንተን የማዕድን ኃብታችንን ሊገድሉት ይፈልጋሉ፡፡ እኔ የኢነርጂ ኩባንያዎቻችንን እመልሣለሁ፤ ሥራን እመልሣለሁ፡፡ ንፁህ የድንጋይ ከሰል የሚባል ነገርም አለ” ሲሉ ክሊንተን ደግሞ “ሕገወጥ ብረቶችን ቻይና ትጥልብናለች፤ ትራምፕ ይገዛቸዋል፡፡ እኔ የሃያ አንደኛው ንፁህ ኢነርጂ ልዕለ-ኃያል እሆናለሁ” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም አንዳችሁ ስለሌላችሁ የምትናገሩት በጎ ነገር አላችሁ? ተብለው ተጠይቀው ሂላሪ ክሊንተን ሲመልሱ “የትራምፕን ልጆች አደንቃለሁ፤ የእርሱን ማንነት ያሳያል” ብለዋል ዶናልድ ትራምፕም “ሂላሪ የቆመችለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ወደኋላ የማትል፤ ተዋጊና የማታፈገፍግ ነች” ብለዋል፡፡