አሜሪካና ሩሲያ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማሻሻልና የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም የሚያስችለውን ሥራ ለመጀመር ተስማምተዋል። ውሳኔው የመጣው የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ሳዑዲ አረቢያ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በአሜሪካና “በሩሲያ መመሪያ ሰጪነት የሚደረግ የጦርነት ማቆም ውሳኔን” እንደማይቀበሉ ተናግረዋል።
በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማቆም ሁለቱም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች በሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት መተው ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ከሩሲያ ልዑክ ጋራ የተወያዩት የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ ዕለቱ የአስቸጋሪውና የረጅሙ ጉዞ አንድ ርምጃ የተወሰደበት ቀን እንደሆነ አመልክተዋል።
“ዛሬ የረጅሙና አስቸጋሪው ጉዟችንን የመጀመሪያ ርምጃ የምንወስድበት ቀን ነው። ነገር ግን እጅግ አስፈላጊ ነው። ፕሬዝደንት ትረምፕ ይህንን ግጭት ለማስቆም ቆርጠዋል። በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ግጭቱ እንዲቆም እንደሚሹ አስታውቀዋል። በሁለት ወይም ሦስት ዓመታት ውስጥ መልሶ ሌላ ግጭት በማይፈጥርበት ሁኔታ ዘላቂ በሆነ መንገድ እንዲቆም ይሻሉ። ይህን መፈጸም ቀላል አይሆንም። ነገር ግን በዓለም ይህን ሂደት ሊያስጀምሩ የሚችሉት እርሳቸው ብቻ ናቸው። ዶናልድ ትረሞፕ ሂደቱን ማስጀመር የሚችሉ ብቸኛ መሪ ናቸው። እናም ዛሬ የሂደቱ የመጀመሪያ ርምጃ የተወሰደበት ቀን ነው” ብለዋል ሩቢዮ።
በንግግሩ ላይ ከተሳተፉት የአሜሪካ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት የዋይት ሃውስ ብሔራዊ የፀጥታ አማካሪ ማይክ ዋልትስ በበኩላቸው፣ በፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕና በሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መካከል የሚደረገው ስብሰባ መቼ እንደሚሆን ቀን እንዳልተቆረጠለት ተናግረዋል።
ድርድሩ ለዩክሬንም ሆነ ለሩሲያ የድንበርና የፀጥታ ማስተማመኛዎች በመሰጠት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ማይክ ዋልትስ አመልክተዋል። ሩሲያ በአሁኑ ወቅት አንድ አምስተኛ የሚሆነውን የዩክሬን ክፍል ትቆጣጠራለች፡፡
አሜሪካ መር የሆነው ጥረት በዩክሬን እና በአውሮፓ በሚገኙ አጋሮች ዘንድ አሳሳቢ በሆነበት በዚህ ወቅት፣ ዋናው ግባቸው “በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑት ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት ያለው” ስምምነት ላይ መድረስ እንደሆነ ማርኮ ሩቢዮ ተናግረዋል።
“ዛሬ ከስብሰባው የወጣሁት፣ በምን መንገድና በምን ፍጥነት ጦርነቱ ይቋጭ በሚለው ላይ የጥረት ሂደቱን ለመጀመር ፍላጎት እንዳላቸው በመተማመን ነው። የሚፈለገው ግብ ላይ የምንደርሰው የግጭቱ ተሳታፊዎች መተው ያለባችውን ጉዳዮች ለመተው ፈቃደኛ ከሆኑ ነው። ይህን ስብሰባ ማድረጉ አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ከሩሲያ ጋራ ባለፉት ሶስት ዓመታታ ይህ ነው የሚባል ውይይት አድርገን አናውቅም” ሲሉ አክለዋል የውጪ ጉዳይ ምኒስትሩ።
ዛሬ ማክሰኞ ከአሶስየትድ ፕሬስ ጋራ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሪቢዮ፣ ሁለቱ ወገኖች፣ ማለትም አሜሪካ እና ሩሲያ በሶስት ጉዳዮች ላይ የተቀመጡ ግቦችን ዳር ለማድረስ እንደተስማሙ አስታውቀዋል። እነዚህም፣ በሞስኮና በዋሽንግተን በሚገኙ ኤምባሲዎቻቸው የነበረውን የሰው ኅይል ቁጥር ወደ ነበረበት መመለስ፣ የዩክሬኑን የሰላም ውይይት ለመደገፍ አንድ ከፍተኛ ቡድን ማቋቋም እንዲሁም ይበልጥ የቀረበ ግንኙነትና የኢኮኖሚ ትብብር ማድረግ የሚሉት እንደሆኑ ሩቢዮ አመልክተዋል።
የሩሲያው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እና ሌሎች ከፍተኛ የሩሲያ ባለሥልጣናት የተሳተፉበት ውይይት የመጀመሪያው መሆኑን እና ወዲፊት ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅም ሩቢዮ አመልክተዋል። በውይይቱ የዩክሬን ባለሥልጣናት እንዳልተገኙ የአሰኦስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ “በአሜሪካና በሩሲያ መመሪያ ሰጪነት የሚደረግን ጦርነት የማቆም ውሳኔን” እንደማይቀበሉ ተናግረዋል። ዜሌንስኪ የሃገራቸው ድንበር በእ.አ.አ 2014 ወደነበረበት እንዲመለስ ሲጠይቁ ቆይተዋል። የአሜሪካ ባለሥልጣናት ግን፣ ዩክሬን ኔቶን ለመቀላቅ እንድምታደርገው ጥረት ሁሉ፣ ድንበሩ ወደነበረበት ይመለስ የሚለው ጥያቄም ተቀባይነት ማግኘቱ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል አስታውቀዋል።
ዜሌንስኪ በዚህ ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት ወደ መጋቢት 1፣ 2017 አስተላልፈዋል። ምክንያቱ ደግሞ የሃገራቸው ባለሥልጣናት በውይይቱ ላይ እንዲካፈሉ ባለመጋበዛቸው እንደሆነ አመልክተዋል። በዚህ ሳምንት ሊያደርጉት የነበረው ጉብኝትም ከውይይቱ ጋራ እንደሚገናኝ ተደርጎ እንዲታይ እንዳልፈለጉም አስታውቀዋል።
ዜሌንስኪ በዩክሬን የአሜሪካ ልዩ ልዑክ የሆኑትን ኪት ኬሎግ ነገ ረቡዕ አግኝተው ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘዋል።
መድረክ / ፎረም