የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ከፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ጋራ ግንኙነታቸውን ማሻሻል ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ ትላንት እሑድ ገልጸው፣ ሀገራቸው ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ ልዩ የኾነ ማዕድን ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ መሆኗን ተናገሩ።
ዜለንስኪ በብሪታንያ ከአውሮፓ መሪዎች ጋራ ከተሰበሰቡ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዩናይትድ ስቴትስ የማዕድን ስምምነቱን ለመፈረም ዝግጁ ትሆናለች ብለው እንደሚያስቡ፤ ነገር ግን “አንዳንድ ነገሮችን ለማጤን ጊዜ ሊያስፈልጋት ይችላል” ብለዋል።
ሁለቱ መሪዎች ባለፈው ሳምንት ዜለንስኪ ዋይት ሐውስን በጎበኙበት ወቅት የስምምነት ውል ይፈራረማሉ ተብሎ ሲጠበቅ የነበረ ቢኾንም፤ ነገር ግን ከትራምፕ እና ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ጋራ በነበራቸው በኃይለ ቃል የተሞላ የቃላት ልውውጥ በኋላ ዝግጅቱ ፈርሷል። ዜሌንስኪ እሑድ ዕለት ዩክሬን የሩስያ የሦስት ዓመት ወረራን ለመዋጋት ለሚደረገው ትግል ዩክሬን በዩናይትድ ስቴትስ ርዳታ ላይ ትተማመናለች ብለዋል።
“እንዲህ ያለውን ርዳታ ማቆም የሩሲያውን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን ብቻ የሚያግዝ ይመስለኛል” ሲሉም አክለዋል። “በዚህ የተነሳም ዩናይትድ ስቴትስ እና የሰለጠነው ዓለም ተወካዮች፣ እንዲሁም የዚህ ዓለም መሪዎች በእርግጠኝነት ፑቲንን አያዙም ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ዐርብ ዕለት በተደረገው ስብሰባ ትራምፕ ዜለንስኪን ምስጋና ቢስ አድርገው የገለጿቸው ሲኾን፤ የማዕድን ስምምነቱ ዩናይትድ ስቴትስ እስካሁን ድረስ ለዩክሬን ለሰጠችው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ርዳታ ካሳ እንዲሆን ሐሳብ አቅርበው ነበር።
ትረምፕ ጦርነቱን የማስቆም አስፈላጊነትን ያስታወቁ ሲሆን፤ የዩናይትድ ስቴተስ ባለሥልጣናት በሳዑዲ አረቢያ ከሩሲያ ሹማምቶች ጋራ ከመገናኘታቸው በተጨማሪም እሳቸውም ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋራ የስልክ ውይይት አድርገዋል።
ትረምፕ “መጨረሻችን እንድ አውሮፓ እንዳይሆን፤ ስለ ፑቲን በመጨነቅ የምናባክነው ጊዜ መቀነስ አለብን፤ ይልቅስ ጊዜያችንን ስደተኞች፣ ስለ አስገድዶ ደፋሪ ቡድኖች፣ አደገኛ መድሃኒቶች፣ ነፍሰ ገዳዮች እና ከአዕምሮ ተቋማት ወጥተው ወደ አገራችን ስለሚገቡ ሰዎች መጨነቅ አለብን” በማለት እሑድ ዕለት ትሩዝ ሶሻል ሚዲያ በተሰኘው ማኅበራዊ መድረክ ላይ አስፍረዋል።
በአንጻሩ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ትላንት እሑድ ዕለት በለንደን በተደረገው እና 18 ሀገራት በተሳተፉበት ውይይት ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምታደርገውን ድጋፍ ላይ እያወላወለች ባለችበት ወቅት አውሮፓ እራሷን “በታሪክ መስቀለኛ መንገድ ላይ አግኝታለች” ሲሉ ተናግረዋል።
አያይዘውም “ይሄ ጊዜ የወሬ ሳይኾን የትግበራ ነው፤ በሕብረት እና በዐዲስ ዕቅድ፣ ለፍትህ እና ለዘለቂ ሰላም ለመሥራት ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል።
ከዋሽንግተን በተለየ መልኩ ዜለንስኪ የካናዳውን ፕሬዝደንት ጀስቲን ትሩዶን ጨምሮ በብዙ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች እና ከኔቶ ዋና ዳይሬክተር ማርክ ሩት ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የዜለንስኪ ደጋፊዎችም ዩክሬንን ለመደገፍ ከስታመርመር መኖሪያ ውጭ ላይ ሰልፍ ወጥተዋል።
የፖላንድ ጠቅላይ ምኒስትር ዶናልድ ቱስክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና አውሮፓ ለሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን “ምዕራቡ ዓለም ለማስፈራሪያቸው እና ለጥቃታቸው የመገዛት ሐሳብ ሀሳብ እንደሌለው” በአንድ ድምፅ እንዲያሳውቅ ጥሪ አቅርበዋል ።
በአጻሩ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ እንደተናገሩት፣ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱ “የግጭቱን ቀጣይነት” ይፈቅዳል ብለዋል።
ፔስኮቭ በተጨማሪም ዜሌንስኪ ለሰላም ፍላጎት ስለሌላቸው ሌላ ሰው "ዜለንስኪን ሰላም እንዲፈልግ ማድረግ አለበት” ብለዋል።
ፔስኮቭ "ዩናይትድ ስቴትስ በአውሮፓ የውጭ ፖሊሲ ላይ የምታደርገው አስደናቂ ለውጥ ከሞስኮ ራዕይ ጋራ የተጣጣመ ነው" በማለት እሑድ ዕለት አስተያየት ሰጥተው ነበር።
እስካሁን ድረስ የተቆረጠ የሰላም ድርድር ቀን የለም።
መድረክ / ፎረም