በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት በቀድሞው የሩስያ መከላከያ ሚንስትር ላይ የእስር ማዘዣ አወጣ


ፎቶ ፋይል፦ የቀድሞው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ እና የሩሲያ ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራል ቫለሪ ገራሲሞቭ በሞስኮ
ፎቶ ፋይል፦ የቀድሞው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ እና የሩሲያ ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራል ቫለሪ ገራሲሞቭ በሞስኮ

ዓለም አቀፍ የወንጀል ችሎት - አይሲሲ በቀድሞው የሩስያ መከላከያ ሚንስትር ሰርጌይ ሾይጉ እና በሩስያው ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራል ቫለሪ ገራሲሞቭ ላይ ዛሬ የእስር ማዘዣ አውጥቷል።

አይሲሲ በመግለጫው ይፋ እንዳደረገው ሁለቱ ተጠርጣሪዎች እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከጥቅምት 2022 እስከ መጋቢት 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ‘የሩስያ ጦር ኃይሎች በዩክሬን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማቶች ላይ ባደረሱት የሚሳኤል ጥቃት ተጠያቂ ስለመሆናቸው በቂ ማስረጃ አለ’ ብሏል። አይሲሲ አክሎም ሾይጉ እና ገራሲሞቭ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶችን በመምራት እና ከመጠን ያለፈ ጉዳት በማድረስም ተጠያቂ ናቸው’ ሲል ሁለቱም በጦር ወንጀል የሚያስከስሱ ድርጊቶች መሆናቸውን ጠቁማል። የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው የግንቦት ወር በአዲሱ አስተዳደራቸው ውስት ባካሄዱት የካቢኔ አባላት ሽግሽግ መሰረት ሾጉን ከመከላከያ ሚንስትር ኃላፊነታቸው ማንሳታቸው ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሁለቱ አገሮች መካከል በቀጠለው ጦርነት ዩክሬን ከሁለቱ ሃገራት ድንበር አቅራቢያ በሚገኙ ሁለት አካባቢዎች በአንድ ለሊት 30 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ያሰማራችበትን የአየር ጥቃት አድርሳለች’ ሲሉ የሩስያ ባለስልጣናት ትላንት አስታውቀዋል።

የሩስያ መከላከያ ሚንስቴር በበኩሉ ‘በቤልጎሮድ ግዛት 29 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በቮሮኔዝ ደግሞ አንድ ሌላ ሰው አልባ አውሮፕላን መትቼ ጥያለሁ’ ብሏል።

የሩሲያ ኃይሎች ባለፉት ቅርብ ወራት ውስጥ በፈጸሙት ወታደራዊ ጥቃት የተቆጣጠሯቸውን ቦታዎች እያሰፉ ከመጡበት የካርኪቭ ግዛት ማዶ የሚገኘው የሩስያው የቤልጎሮድ ግዛት የዩክሬን ተደጋጋሚ አየር ጥቃት ኢላማ መሆኑ ይታወቃል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG