የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትላንት ማክሰኞ በይፋ ባልተገለጸ ድንገተኛ ጉብኝት ዩክሬን በመግባት፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናት “ጠንካራ ማስተማመኛ” ብለው የጠሩትን መልዕክት ማድረሳቸው ታውቋል። ብሊንከን ኪቭ የገቡት የዩክሬን ኃይሎች በምሥራቅ የሃገሪቱ ክፍል ከሩሲያ ሠራዊት ጋራ ከፍተኛ ፍልሚያ ላይ በሚገኙበትና ከአጋሮቻቸው የመሣሪያ ዕርዳታ በሚጠባበቁበት ወቅት ነው።
ብሊንከን ከሃገሪቱ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌኒስኪ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከውጪ ጉዳይ ሚኒክስትሩ ጋራ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል።
ብሊንከን በቆይታቸው በጦር ሜዳ ስላለው ውሎ ወቅታዊ መረጃን፣ አሜሪካ በፀጥታና ኢኮኖሚ መስክ ያደረገችው ርዳታ ያመጣውን ውጤት፣ ዘላቂ የሆነ የፀጥታና የኢኮኖሚ ትብብርን እንዲሁም የዩክሬንን ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ ለማድረግ በመካሄድ ላይ ስላለው ጥረት በተመለከተ እንደሚነጋገሩ የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር አስታውቀዋል።
አሜሪካ ባለፈው ዓርብ የ400 ሚሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ ዕርዳታ ለዩክሬን መላኳን አስታውቃለች፡፡
ሩሲያ በካርኪቭ ክልል በምድር በማድረስ ላይ ያለቸውን ጥቃት ለመመከት ማድረግ በሚቻለው ሁሉ መሣሪያ በአስቸኳይ ለዩክሬን እንደሚላክ ዋይት ሃውስ ሰኞ ዕለት አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም