በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፈረንሳይ እና ዩክሬን የጸጥታ ትብብር ስምምነት ሊፈራረሙ ነው


ፎቶ ፋይል፦ የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ እና የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኢማኑዌል ማክሮን በኬየቩ፣ ዩክሬን እ አ አ ሰኔ 16/2022
ፎቶ ፋይል፦ የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ እና የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኢማኑዌል ማክሮን በኬየቩ፣ ዩክሬን እ አ አ ሰኔ 16/2022

የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ዛሬ ፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ገብተዋል። ሁለቱ ሀገሮች የጸጥታ ጉዳይ ስምምነት እንደሚፈራረሙ የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኢማኑዌል ማክሮን ፅሕፈት ቤት ትናንት ሐሙስ አስታውቋል። የስምምነቱን ዝርዝር ይዘት ግን አልገለጸም።

ዜሌንስኪ ወደፓሪስ የተጓዙት በርከት ያሉ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በሚካሄዱበት በዚህ ሳምንት ሲሆን ነገ ቅዳሜ ጀርመን ውስጥ በሚከፈተው የሚዩኒክ የጸጥታ ጉባዔ ላይም ይገኛሉ።

የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሐገሮች የመከላከያ ሚንስትሮች ለዩክሬን የሚሰጠው ድጋፍ መቀጠል ስለሚችልበት መንገድ ትናንት ሐሙስ ብረሰልስ ላይ ተሰብስበው ተወያይተዋል።

የኔቶ ዋና ጸኅፊ ዬንስ ስቶልትንበር ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ዩክሬን የሚያስፈልጋትን የጦር መሣሪያ፥ ጥይት እና ሌላም አቅርቦት ማግኘቷን ለማረጋገጥ የመከላከያ ምርታችንን ማሳደግ አለብን ብለዋል።

አንድ ሚሊዮን አብራሪ አልባ አውሮፕላኖችን ለዩክሬን ለመስጠት በሕብረት እየሰሩ ያሉ የኔቶ አባል ሐገሮች እንዳሉ ዋና ጸሐፊው አመልክተዋል። የተቀበሩ ፈንጂዎችን ለማንሳት በትብብር ለመስራት ያቀዱ ሀያ ሐገሮች ያሉ መሆኑን የገለጹት ስቶልትንበርግ ይህ ሁሉ ድጋፍ የሚደረገው የዩክሬናውያንን ሕይወት ከሞት ለመታደግ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለዩክሬን ከሚሰጠው አጠቃላይ የጦር መሣሪያ እርዳታ ውስጥ ዘጠና ዘጠኝ ከመቶውን የሚለግሷት የኔቶ አባል ሐገሮች መሆናቸውን የሕብረቱ ዋና ጸሐፊ አስታውሰዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤትም ለዩክሬን የታቀደውን እርዳታ ያጸድቃል ብለው እንደሚጠብቁ የኔቶው ዋና ጸሐፊ አንስተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ትልቋ የዩክሬን አጋር እንደመሆኗ ድጋፏን መቀጠል አለባት ያሉት የኔቶው ዋና ጸሐፊ ፈጥነው ውሳኔ ይሰጣሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ዩክሬንን ድጋፍ የምንሰጠው ለበጎ አድራጎት ብለን ሳይሆን ለራሳችንም ደህንነት ብለን ነው ሲሉ አስረድተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG