ሩሲያ "ዓላማቸውን በሚመቱ የረጅም ርቀት ከባድ መሣሪያ ጥቃቶች ከግንባር በስተጀርባ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባት ነው" ሲል የብሪታንያ የመከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ (ዓርብ) አመለከተ።
የዛሬ ሁለት ሣምንት ግድም፤ ጥቅምት 30 ኼርሶን ወረዳ ውስጥ ከግንባር 23 ኪሎሜትር በስተጀርባ በምትገኝ ህላድኪቭካ መንደር በከባድ ተሽከርካሪዎች ቅፍለት ላይ በተፈፀመ ጥቃት ከሰባ በላይ የሩስያ ወታደሮች መገደላቸውን ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።
የሚኒስቴሩ ሪፖርት አክሎ ባለፈው ዕሁድ፤ ኅዳር 9 ደግሞ ከውጊያው ግንባር 60 ኪሎ ሜትር በስተጀርባ በሚገኘው ኩማቾቭ ሲካሄድ በነበረ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ወይም የሙዚቃ ትርዒት ላይ የደረሰ ድብደባ ምናልባት በአሥሮች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ሳያደርስ እንዳልቀረ ተናግሯል።
ዩክሬን ራሷም ብትሆን ከባድ ጉዳት እንደደረሰባት የሚጠቁመው ይህ ሪፖርት ባለፈው ጥቅምት 23 በተካሄደ የሜዳልያ ሥነ ሥርዓት ላይ የተተኮሰ የሩሲያ ሚሳይል 19 የአንድ የዩክሬን ብርጌድ ባልደረቦችን መግደሉን አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ ምሥራቃዊቱን አቭዲቭካን ለሣምንታት ያለማቋረጥ ከደበደበች በኋላ አሁን ወታደሮቿን ወደ ፈራረሰችው፣ ግን ገዥ መሬት ወደሆነችው ከተማ በገፍ እያሰማራች መሆኑን፤ ይሁን እንጂ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባት ከፍተኛ ባለሥልጣናቱና ወታደሮች ትናንት አመልክተዋል።
ሩሲያ ከጥቅምት አጋማሽ አንስቶ ከተማዪቱን ለመያዝ በብዙ መጣሯንና የሚያጠረቃ ስኬት አለመቀዳጀቷን ዩክሬናዊያኑ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም