በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩክሬን ጦርነት ዓመት ሞላው፤ ዜሌንሲኪ "ድል እናደርጋለን" አሉ


ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ
ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ

የዩክሬኑ ጦርነት ከተጀመረ ዛሬ እአአ የካቲት 24 አንድ ዓመት ሞላው። ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ዛሬ በቴሌቭዥን ባደረጉት ንግግር "በጦርነቱ ድል እናደርጋለን" ብለዋል።

"ድል እናደርጋቸዋለን። ምክንያቱም ዩክሬናውያን ነን እና። የዛሬ ዓመት የካቲት 24 በዘመናዊ ታሪካችን ፈታኙ የመከራ ቀን እንደዚህ ነው የጀመረው። ያን ቀን ሌሊት የነቃን እስከዛሬ አልተኛንም። የሩስያ ነፍሰ ገዳዮች ፍርዳቸው እስኪያገኙም፣ ፈጽሞ ዕረፍት አይኖረንም።

ከዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት፣ ከእግዚአብሄር፣ ከአርበኞቻችን ቅጣታቸውን ይቀበላሉ። ፍርዱ ምን እንደሚሆን ግልጽ ነው። የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ወርራን የነበረችው ጎረቤት ሀገር የዛሬ ዓመት ነፍሰ ገዳይ፣ ዘራፊ፣ አሸባሪ ሆና ተመለሰች። መጠየቃቸው አይቀርም። እሱ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ድል እንደምናደርጋቸውም አንጠራጠርም” ብለዋል፡፡

ዜሌንስኪ በሩሲያ በተያዙት የሀገራቸው ግዛቶች ላሉት ዩክሬናውያን ባሰሙት ንግግራቸው "አልረሳናችሁም። ግዛታችንን በሙሉ ነጻ እናወጣለን። ሳትወዱ በግድ ወደውጭ ሀገር የተሰደዳችሁ ሁሉ ወደሀገራችሁ እንድትመለሱ የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ እና ዩክሬን ተኩስ አቁመው የሰላም ድርድር እንዲጀምሩ ቻይና ጥሪ አቅርባለች። ቻይና ባቀረበችው ባለ 12 ነጥብ ሃሳብ ምዕራባዊያን ሩሲያ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ ጠይቃለች። በተጨማሪም በሲቪላዊ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ለመከላከል የኒውክሊየር ጣቢያዎችን ደሕንነት ለመጠበቅ እና ሰብዓዊ ዕርዳታ ማጓጓዣ ኮሪደሮችን ለመክፈት የሚሆኑ ሀሳቦችን አቅርባለች።

ቻይና በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ገለልተኛ ሆና ለመታየት ስትሞክር ቆይታለች። ሆኖም የሩሲያን ወረራ ለማውገዝ ፈቃደኛ ሳትሆን ቆይታለች።

በሌላ በኩል ትናንት ዋይት ሀውስ በሩሲያ እና እና አውሮፓ ውስጥ በጦርነቱ ተዋናይ በሆኑ ሦስተኛ ሀገሮች ላይ ያነጣጠሩ ላይ ስፋት ያለው አዲስ ማዕቀብ እንደሚደነግግ ዛሬ አስታውቋል።

በባንኮች፣ ማዕድን እና የመከላከያ ዘርፎች ላይ እንደሚያነጣጥር ያስታወቀው ዋይት ሐውስ ሩሲያ፣ አውሮፓ፣ እስያ እና መካከለኛው ምስራቅ ባሉ የሩስያን ወረራ በሚደግፉ 200 ግለሰቦች ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጣል አመልክቷል።

በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የ2 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ዕርዳታ እንደምትሰጥም ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

በተያያዘ ዜና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትናንት ሐሙስ ባሳለፈው ውሳኔ የሩሲያ ወታደሮች ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ከዩክሬን ግዛት እንዲወጡ ጠይቋል።

XS
SM
MD
LG