ሩሲያ ዛሬ ሰኞ በርካታ የዩክሬን ከተሞችን መደብደቧንና ከኢላማዎቹ መካከል የመሰረተ ልማት አገልግሎት ተቋማት እንደሚገኙበት የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ ያካሄደቸው መጠነ ሰፊ ጥቃት ከ50 በላይ ክሩዝ ሚሳዬሎች የሚገኙበት መሆኑን የዩክሬን ጦር በማህበራዊ መገናኛው መድረክ ቴሌግራም ላይ ባስተላለፈው መልዕክት አስታውቋል፡፡
ጥቃቱ የዋና ከተማዪቱን የተወሰነ ክፍል የመብራትና የውሃ አቅርቦት ማቋረጡን የኪየቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊትስኮ ተናግረዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ምክትል ሹም ካይረሎ ታይመሰንኮ የሩሲያ ሚሳዬሎች በበርካታ የዩክሬን ግዛቶች የሚገኙ የመብራት ኃይል መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ በኃይል የያዘችው ክሬሚያ አቅራቢያ ባለው ጥቁር ባህር ላይ የነበሩ መርከቦችን አጥቅታለች ስትል ዩክሬንን ከሳለች፡፡
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድሚትሮ ኩሌባ ለዚህ ክስ መልስ በሚመስል ንግግራቸው ጥቃቶቹን “ኃላፊነት የጎደላቸው እና “አጸፋ” ተብለው የሚጠሩም አይደሉም” ብለዋል፡፡
ኩሌባ ባስተላለፉት የትዊት መልዕክትም “ሩሲያ በጦር ሜዳ ከመዋጋት ይልቅ፣ ሰላማዊ ሰዎችን ትወጋለች” ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም “ሩሲያ ይህን የምታደርገው አሁን ድረስ ሚሳዬሎቹና ዩክሬናውያንን የመገደል ፈቃዱ ስላላት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡