በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢራን ለሩሲያ የምትልከውን መሣሪያ በተመለከተ የፀጥታው ም/ቤት እንዲነጋገርበት ተጠየቀ


ዩናይትድ ስቴትስ፣ እንግሊዝ እና ፈረንሣይ፣ ሩሲያ ኢራን-ሠር የሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በዩክሬኑ ጦርነት እየተጠቀመች ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ የተባብሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ም/ቤት አጀንዳ ይዞ እንዲነጋገርበት ጠይቀዋል።

ዲፕሎማቶች እንዳመለከቱት ሃገሮቹ ያቀረቡት ጥያቄ አንድ የመንግሥታቱ ድርጅት ኃላፊ የዝግ ስብሰባ በሚካሄድበት ወቅት በጉዳዩ ላይ ቀርበው በማብራሪያ እንዲሠጡ የሚለውን ይጨምራል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት እንዳመለከቱት ባለፈው ሳምንት ዋና ከተማይቱን ኪየቭን ጨምሮ አካባቢውን ሲደበድቡ የሰነበቱት ሰው አልባው አውሮፕላኖች ሩስያ በቦምብ እና በኢላማዎቿ ላይ የተነጣጠረ ጥቃት ለማድረስ የተጠቀሙባቸው ኢራን-ሠር የሆኑት ሻሂድ -136 ድሮኖች ናቸው።

ይሁን እንጂ ኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖቹን ለሩሲያ ማቀበሏን ትክዳለች፤ ሩሲያም በተመሳሳይ ሰው አልባው አውሮፕላኖቹን አልተጠቀምኩም ባይ ነች።

በሌላ ዜና የኢስቶኒያ መከላከያ ሚኒስትር ሃኖ ፔቭኩር ለዜና ሠዎች ትናንት እንደተናገሩት በበርካታ የዩክሬን ከተሞች ላይ የድሮን ጥቃት ይኖራል ብለን እንጠብቃለን ብለዋል።

ዩክሬን ሩስያ ካሰማራቻቸው ከእነኚህ ሰው አልባው አውሮፕላኖች ገሚሱን መትታ መጣሏን፣ ሆኖም አሁንም ተጨማሪ ርዳታ እንደሚያስፈልጋት ፔቭኩር ጨምረው አመልክተዋል። የዩክሬን ባለሥልጣናት የአየር መቃወሚያዎችን በተመለከተ ርዳታ እንዲደረግላቸው ካሁንቀደም ለአጋሮቻቸው ያቀረቡትን ተማጽኖ ሰሞኑንም ደግመው አሰምተዋል። ከመቶ በላይ የሚሆኑ ኢራን ሠር የሆኑ ድሮኖች በኃይል ማመንጫዎች፣ በውሃ ማጣሪያዎች፣ በመኖሪያ ሕንፃዎች፣ በድልድዮች እና ሌሎች ኢላማዎች ላይ ማረፋቸውን የዩክሬን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ኃላፊ አንድሪ የርማክ፣ ሩሲያ የዩክሬን ጦር ኬርሶን ክልልን ሊደበድብ ነው በሚል የሃሰት መልዕክት ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ በፕሮፖጋንዳ ሕዝቡን እያሸበረች ነው ሲሉ ወንጅለዋል።

በዩክሬን የሩሲያው አዲሱ ወታደራዊ አዛዥ ሰርጌ ሱሮቪኪን ሩሲያ-24 ለተባለው መንግስታዊ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ዩክሬን ድብደባ ከመፈጸሟ በፊት ሩሲያ በኬርሶን ያሉ ሰዎችን ለማስወጣት አቅዳለች።

ኬርሶን በቅርቡ በተደረገ ሕዝበ-ውሳኔ ሩሲያ ከጠቀለለቻቸው አራት ክልሎች አንዷ ነች። ይሁን እንጂ ሕዝበ ውሳኔውንና ግዛት ነጠቃውን ዩክሬንና አጋሮቿ ተቃውመውታል።

XS
SM
MD
LG