በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሩሲያ የዩክሬን መዲናን በሚሳዬል ደበደበች


በፍንዳታው ከጥቅም ውጭ የሆኑ ተሽከርካሪዎች፤ ኪየቩ፣ ዩክሬን
በፍንዳታው ከጥቅም ውጭ የሆኑ ተሽከርካሪዎች፤ ኪየቩ፣ ዩክሬን

ሩሲያ ዛሬ ሰኞ የዩክሬንን መዲና ኪየቭንና ሌሎች ከተሞችን በሚሳዬል ደብድባለች። የዩክሬን ባለሥልጣናት እንዳሉት 75 ሚሳዬሎች ወደ ዩክሬን ተወንጭፈው የነበረ ሲሆን፣ አርባ አንዱን መትተው ጥለዋል።

የመዲናዋ ኪየቭ ፖሊስ እንዳለው አብዛኛው ሚሳዬሎች ከተማዋ መካከል ሲያርፉ፣ ቢያንስ 5 ሰዎች ሞተው 12 ቆስለዋል። ሰው በብዛት የሚገኝባቸውን ፓርኮችና የቱሪስት መስህቦችም ኢላማ ነበሩ ተብሏል።

በምዕራብ የምትገኘው ለቪቭ ከተማ፣ ማዕከላዊዋ ኒፕሮ፣ እና ምሥራቃዊቷ ካርኪቭ ከተሞችም ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።

ሩሲያ የሲቪል አካባቢዎችንና የኃይል መስመሮችን በመላ ሃገሪቱ ኢላማ ያደረገችው “ድንጋጤና ትርምስ” ለመፍጠር ነው ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ አክለውም የግሩፕ 7 አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ንግግር እንደሚደርጉና፣ ጉዳዩን በተመለከተም ከጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ እና ከፈረንሳዩ ፕሬዝደንት አማኑኤል ማክሮን ጋር እንደተነጋገሩ አስታውቀዋል።

ከማክሮን ጋር ከተገናኙ በኋላ ዜሌንስኪ በላኩት የትዊተር መልዕክት፣ “የአየር መከላከያችንን ስለምናጠናክርበት፣ ከአውሮፓ እንዲሁም ከዓለም ጠንካራ ምላሽ ስለሚሰጥበት እና የሩሲያ ፌዴሬሽን ላይ ጫና ስለሚፈጠርበት ሁኔታ ላይ ተነጋረናል” ብለዋል።

የማክሮን ቢሮ በብኩሉ፣ ወታደራዊን ጨምሮ ፈረንሳይ ለዩክሬን ስለምታደርገው ዕርዳታ ቃሏን አድሳለች ብሏል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለሃገራቸው የፀጥታ ምክር ቤት እንደተናገሩት፣ የሚሳዬል ድብደባው የዩክሬንን የሃይል አውታሮች፣ ወታደራዊና የመገናኛ መሠረተ ልማቶችን ኢላማ ያደረገ ሲሆን፣ ቅዳሜ ዕለት ሩሲያን ከክሪሚያ በሚያገናኘው ድልድይ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የመልስ ምት ነው ብለዋል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት ድልድዩን በከፊል ላፈረሰው ጥቃት ኃላፊነት አልወሰዱም። “ድርጊቱ በዩክሬን የሥለላ ቢሮ የተወጠነ፣ የተቀነባበረና የተፈጸመ ነው” ሲሉ ፑቲን ተናግረዋል።

ከርች ድልድይ ሩሲያን ከክሪሚያ ጋር የሚያገናኝ ሲሆን፣ ሩሲያ በደቡብ ዩክሬን ለምታካሂደው ጥቃት ለወታደራዊና ሌሎች አቅርቦቶች የሚውል መተላለፊያ ነው።

XS
SM
MD
LG