በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፑቲን ተጠባባቂ ኃይላቸውን እንደሚያንቀሳቅሱ አስታወቁ


የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

በሰሜን ዩክሬን የሩሲያ ኃይሎች በተከፈተባቸው የመልሶ ማጥቃት በርካታ ቦታዎችን እንዲለቁ ከተገደዱ በኋላ፣ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሀገራቸውን ተጠባባቂ ወታደራዊ ኃይል በከፊል እንደሚያንቀሳቅሱ አስታውቀዋል።

ፑቲን በቴሌቭዥን ባስተላለፉት መልዕክት የተጠባባቂ ኃይሉን ማንቀሳቀስ የሃገሪቱን ግዛትና ሉአላዊነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ በበኩላቸው 300 ሺህ የሚሆኑ ተጠባባቂዎችን ጦሩ እንደሚጠራ አስታውቀዋል።

ፑቲን በመልዕክታቸው የምዕራቡ ዓለም ሩሲያን ለማዳከምና ለማውደም መነሳቱን በመጠቆም “ሩሲያንና ሕዝቧን ለመከላአከል በእጃቸን የሚገኘውን ማንኛውንም አማራጭ እንጠቀማለን” ብለዋል፡፡

ምዕራቡ ዓለም በሚከተለው ሩሲያ ጠል ፖሊሲ እያንዳንዱን መስመር ተላልፏል” ያሉት ፑቲን፣ “በኑክሌር መሳሪያ ሊያሰፈራሩን የሚሞክሩት ወገኖች የነፋስ መጠቆሚያው ወደ እነርሱ ዞሮ ሊያሳይ እንደሚችልም ማወቅ አለባቸው” ብለዋል።

የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝደንት ቻርለስ ሚሼል በትዊተራቸው እንዳሉት ፑቲን መግለጫውን የሰጡት ሀገራት ለተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ተሰባስበው “ለትብብር፣ ጸጥታ፣ እና ብልጽግና በመሥራት ላይ ባሉበት ወቅት ነው።”

“በዚህ ጦርነት ያለው አንድ ወራሪ ሩሲያ፣ የተወራሪው ደግሞ ዩክሬን ነው” ያሉት ሚሼል “የአውሮፓ ኅብረት ለዩክሬን የሚያደርገው ድጋፍ የማያወላውል ነው” ሲሉ አክለዋል።

ፑቲን በንግግራቸው ሰባት ወራትን ያሰቆጠረው የዩክሬን ወረራ ዓላማ ዶንባስ ክልልን “ነጻ” ማውጣት ሲሆን፣ እዚያ የሚገኙ ሰዎች የዩክሬን አካል ሆኖ መቀጠል አይፈልጉም ብለዋል።

ዶንባስ ውስጥ በሞስኮ ቁጥትር ስር ያሉት የሉሃንስክ እና ዶነትስክ ተገንጣይ መሪዎች የሩሲያ አካል መሆናቸውን ለማወጅ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ድምጽ ይሰጣል ሲሉ ትናንት አስታውቀዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ “ሩሲያ የሃሰት ሪፍረንደም ልትተውን ሙከራ ላይ ነች” ሲሉ አጣጥለውታል።

ዋይት ሃውስ የሪፈረንደሙን ዕቅድ ወዲያውኑ ተቃውሞታል። በጦር ሜዳው ድል ያልቀናት ሞስኮ ወታደሮችን ከነዝያ ክልሎች ለመመልመል የምታደርገው ጥረት ሳይሆን አይቀርም ሲል ዋይት ሃውስ አስታውቋል።

“ቦታዎቹ የዩክሬን አካል በመሆናቸው ሪፈረንደሙ የድንበርና የሉአላዊነት መርህዎችን የሚጥስ ነው” ሲሉ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ የሂኑት ጄክ ሱሊቫን ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG