በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩክሬን ኢዚየም ከተማ የጅምላ መቃብር ተገኘ


በዩክሬን ኢዚየም ከተማ የጅምላ መቃብር ተገኘ
በዩክሬን ኢዚየም ከተማ የጅምላ መቃብር ተገኘ
  • አሜሪካ ተጨማሪ የጦር መሣሪያ ለዩክሬን ልትሰጥ ነው

አራት መቶ አርባ አስከሬኖችን የያዘ የጅምላ መቃብር በሰሜን ምሥራቅ ዩክሬን በምትገኘውና በቅርቡ የዩክሬን ኃይሎች ከሩሲያ ኃይሎች ነጥቀው በተቆጣጠሯት ኢዚየም በተባለች ከተማ እንዳገኙ የዩክሬን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የዩክሬን ኃይሎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የመልሶ ማጥቃት ከጀመሩ በኋላ የሩሲያ ኃይሎችን ከካርኪቭ አካባቢ ገፍተው አስወጥተዋል። የሩሲያ ኃይሎች በርካታ መሣሪያዎችንና ሌሎች የጦር መገልገያዎችን ጥለው ሄደዋል ሲሉ የዩክሬን ባለሥልጣናት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

“ይህ ነፃ ካወጣናቸውና በትልቁ ከተማ ካገኘናቸው የጅምላ መቃብሮች ሁሉ ትልቁ ነው። 440 ሰዎች በአንድ ቦታ ተቀብረዋል። እንዳንዶቹ በመድፍ ጥቃት ሲገደሉ ሌሎቹ ደግሞ በአየር ጥቃት የተገደሉ ናቸው” ሲሉ የካርኪቭ አካባቢ የፖሊስ ምርመራ ኃላፊ ሰርሂይ ቦልቪኖ ለስካይ ኒውስ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት የሚሉትን በገለልተኛ ወገን ማጣራት አለመቻሉንና፣ በሩሲያ ወገን ወዲያውኑ የተሰጠ አስተያየት አለመኖሩን ሮይተርስ ጨምሮ ዘግቧል።

በቅርቡ የዩክሬን ኃይሎች መልሰው በተቆጣጠሯት ኢዚየም ከተማ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሩሲያን ተጠያቂ አድርገዋል። ድርጊቱንም ቡቻ በተባለው የዋና ከተማዋ ኪየቭ ክፍል በወረራው መጀመሪያ ወር ላይ ከተገኘው ሌላ የጅምላ መቃብር ጋር አመሳስለውታል።

ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ
ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ

“ሩሲያውያኑ ለቀው በሚወጡት ቡታ ሁሉ እልቂትን ፈጽመው አየሄዱ በመሆኑ ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ሲሉ ዜሌንስኪ ዛሬ ሐሙስ በቪዲዮ ባሰርጩት መልዕክት ተናግረዋል።

ዩክሬንና ምዕራባውያን አጋሮቿ ሩሲያ የጦር ወንጀል ፈጽማለች ሲሉ ይከሳሉ። ሩሲያ በበኩሏ ሲቪሎችን ኢላማ አለማድረጓንና የጦር ወንጀል አለመፈጸሟን ትናገራለች።

የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬ ውሎው የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በቪዲዮ ንግግር እንዲያደርጉ ለማስቻል ድምፅ ይሰጥል ተብሎ ይጠበቃል። ጉባዔው ዘንድሮ ሁሉም መሪዎች ንግግራቸውን በአካል መጥተው እንዲያሰሙ ቢፈልግም፣ በድምፅ ብልጫ ፈቃድ ያገኙ ግን በቪዲዮ ንግግራቸውን ማቅረብ ይችላሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተጨማሪ 600 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የቶር መሳሪያ ለዩክሬን እንደሚሰጥ አስታውቀዋል። ነጩ ቤተ መንግሥት እንዳስታወቀው፣ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ካለው ክምችት ላይ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ ሲለግስ ለ21ኛ ግዜ መሆኑ ነው።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የተከማቸ ትርፍ የጦር መሣሪያን ለሌላ ወገን የማስተላለፍ ህጋዊ መብት አላቸው።

XS
SM
MD
LG