የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጦራቸው ከሩሲያ ወታደሮች መልሶ የነጠቃትን ኢዚየም ከተማን ጎብኝተው ወታደሮቻቸውን አበረታተዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ከሰባት ወራት በኋላ፣ የዩክሬን ኃይሎች የመልሶ ማጥቃት በማካሄድ በሰሜን ምስራቅ ዩክሬን የሚገኘው የካርኪቭ አካባቢ የሚገኙ ሰፋፊ ቦታዎችን መልሰው ተቆጣጥረዋል።
የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ዕርሰላ ቮንደር ለየን ዛሬ ወደ ዩክሬን በመጓዝ ኪየቭ ውስጥ ከዜሌንስኪ ጋር ተገናኝተው አውሮፓ ለዩክሬን ስለምታደርገው ድጋፍ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
“አውሮፓ ለዩክሬን ያላት ድጋፍ የማይናወጥ ነው” ሲሉ ቮንደር ለየን ዛሬ የአውሮፓ ህብረት ሁኔታን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ላይ ተደምጠዋል ።
የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ እንዳስታወቀው ደግሞ፣ ሩሲያ ምናልባትም ለመጀመሪያ ግዜ፣ በኢራን የተሰሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ሳትጠቀም አልቀረችም። ዩክሬን በበኩሏ በኢራን የተሰራ ድሮን መትታ መጣሏን አስታውቃለች።