በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

‘ሩሲያ በዩክሬን ሲቪል ተቋማት ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች’ ስትል አሜሪካ አስጠነቀቀች


የዩክሬን የክብር ዘበኛ ወታደሮች በባንዲራ ቀን የዩክሬን ባንዲራ ከፍ ሲያደርጉ ይታያል፤ ኪዪቭ፣ ዩክሬን
የዩክሬን የክብር ዘበኛ ወታደሮች በባንዲራ ቀን የዩክሬን ባንዲራ ከፍ ሲያደርጉ ይታያል፤ ኪዪቭ፣ ዩክሬን

“በዩክሬን ሲቪል ተቋማትና የመንግሥት አገልግሎቶች ላይ በሚቀጥሉት ቀናት ጥቃት ለማድረስ ሩሲያ ዝግጅት እያደረገች ነው” ስትል አሜሪካ አስጠንቅቃለች።

ይህ ኪዪቭ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ማስጠንቀቂያ “የሃገራቸንን የነፃነት ቀን አስታክካ ሩሲያ ጥቃት ልትሠነዝር ትችላለች” ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ከቀናት በፊት ያሉትን ተከትሎ የወጣ መሆኑን በሥፍራው የሚገኙ የአሜሪካ ድምፅ ሪፖርተሮች ዘግበዋል።

“ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈፅመው ጥቃት ለሲቪሎችና ሲቪል ተቋማት አደጋ መጋረጡን ቀጥሏል” ያለው የኤምባሲው መግለጫ የአሜሪካ ዜጎች ከቻሉ ዩክሬንን ለቅቀው እንዲወጡ አሳስቧል።

ዩክሬን ከሶቪየት ኅብረት መበተን በኋላ እራሷን የቻለች ሃገር ከሆነች ነገ፤ ረቡዕ ነኀሴ 18 ሰላሣ አንድ ዓመት የሚሞላ ሲሆን የሩሲያ ወረራ ደግሞ ስድስተኛ ወሩን ይይዛል።

ማስጠንቀቂያዎቹን ተከትሎ በኪዪቭ ውስጥ ሊደረጉ የታቀዱ የነፃነት ቀን ዝግጅቶች ተሠርዘዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፖላንድ ፕሬዚዳንት አንድሬ ዱዳ ዛሬ ወደ ኪዪቭ ሄደው ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ድጋፍ ለዩክሬን ስለሚሰጥበት ሁኔታ ከዜሌንስኪ ጋር ተወያይተዋል።

ሌሎች ሃገሮች እርዳታ እንዲያደርጉ ፖላንድ መጎትጎትና ማሳመን በምትችልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሁለቱ መሪዎች እንደሚነጋገሩ የዱዳ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የሩሲያ ኃይሎች በዛፖሪዥዢያ አዲስ ጥቃት መክፈታቸውን የዩክሬን ጦር ያስታወቀ ሲሆን ይህም እዚያ ያለውን በአውሮፓ ትልቁን የኒኩሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ደኅንነትን በተመለከተ ሥጋት እንዲጨምር አድርጓል።

ባለፉት ስድስት ወራት በጦርነቱ ውስጥ ዘጠኝ ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቿ እንደተገደሉባት ዩክሬን ትናንት ሰኞ አስታውቃለች።

በዚህ ጊዜ ውስጥ 5 ሺህ 500 ሲቪሎች መገደላቸውን ማረጋገጡን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያመለከተ ሲሆን የድርጅቱ የህፃናት መርጃ ተቋም (ዩኒሴፍ) ደግሞ ከ972 በላይ ህፃናት መገደላቸውን ወይም ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል።

XS
SM
MD
LG