በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩክሬናዊያን ምርኮኞች በከባድ መሣሪያ ድብደባ መገደላቸውን ሩሲያ ተናገረች


 ዩክሬናዊያን ምርኮኞች በእስር ቤት ውስጥ በከባድ መሣሪያ ድብደባ መገደላቸውን በሩሲያ የሚደገፉ ተገንጣዮች ተናገሩ። በእሳት የተቃጠሉ በላስቲክ ተሸፍኖ ይታያል፤ ኦሌኒቭካ፣ ዶኔትስክ ክልል፣ ዩክሬን እአአ ሐምሌ 29/2022
ዩክሬናዊያን ምርኮኞች በእስር ቤት ውስጥ በከባድ መሣሪያ ድብደባ መገደላቸውን በሩሲያ የሚደገፉ ተገንጣዮች ተናገሩ። በእሳት የተቃጠሉ በላስቲክ ተሸፍኖ ይታያል፤ ኦሌኒቭካ፣ ዶኔትስክ ክልል፣ ዩክሬን እአአ ሐምሌ 29/2022

በማሪዮፖሉ ውጊያ የተያዙ ቢያንስ አርባ ዩክሬናውያን ምርኮኞች “የዩክሬን ተዋጊዎች በሃገሪቱ ምሥራቃዊ አካባቢዎች አደረሱ” ብሉት የከባድ መሣሪያ ድብደባ መገደላቸውን በሩሲያ የሚደገፉ ተገንጣዮች ተናገሩ።

ሌሎች ሰባ አምስት የሚሆኑ ምርኮኞችም መቁሰላቸውን አመልክተዋል።

ምርኮኞቹ በማሪዮፖል የብረታ ብረት ፋብሪካ ውስጥ መሽገው የሩሲያን ጥቃት ለሦስት ወራት ከመከቱ በኋላ ከተማረኩት መካከል መሆናቸው ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የብሪታኒያ የመከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ በትዊተር ባወጣው የደኅንነት መረጃ “ግዙፍ ለውጥ” ባለው እርምጃ ሩሲያ ከውጊያ ግንባር እንቅስቃሴዎቿ ከፊሉን ኃላፊነት “ቫግነር ግሩፕ” ለሚባለው የግል ወታደራዊ ኩባኒያ እንዳዛወረች አመልክቷል።

ሚኒስቴሩ በዚሁ ትዊቱ “የሩሲያ መንግሥት ይህንን ማድረጉ ቫግነር ግሩፕን ከመሳሰሉ ኩባንያዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ማስተባበል እንዳይችል ያደርገዋል” ብሏል።

ሩሲያ እርምጃውን የወሰደችው የበረታ የእግረኛ ተዋጊ እጥረት ስላለባት ሳይሆን እንደማይቀርም ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።

በተያያዘ ዜና የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በትናንቱ ዕለታዊ ንግግራቸው "በዓለም ላይ የሩሲያን ያህል ዓቅሙን ሽብርተኛነት ላይ የሚያውል ሌላ የለም” ብለዋል። "ዓለምአቀፍ የሆነ የህግ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሩሲያን በሽብር ደጋፊ መንግሥትነት እንዲፈርጃት የሚጠይቀውን ውሳኔ የዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በሙሉ ድምጽ በማሳለፋቸው ዘሌንስኪ አመስግነዋል።

ሩሲያ ትናንት በሣምንታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዩክሬይን ዋና ከተማ ክዪቭ አካባቢና ሰሜናዊ ቼርኒሂቭ ክፍለግዛት ላይ የሚሳይል ድብደባ ማድረሷ ተዘግቧል።

XS
SM
MD
LG