በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሀገሮች ሩሲያ ላይ አዳዲስ ማዕቀቦች በመደንገግ ላይ ናቸው


የእሳት አደጋ ሠራተኞች በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ የደረሰውን ፍንዳታ ተከትሎ እርዳታ እየሰጡ ኪየቩ፣ ዩክሬን እአአ ሰኔ 26/2022
የእሳት አደጋ ሠራተኞች በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ የደረሰውን ፍንዳታ ተከትሎ እርዳታ እየሰጡ ኪየቩ፣ ዩክሬን እአአ ሰኔ 26/2022

ሞስኮ ዩክሬን ላይ እያካሄደች ባለው ጦርነት የተነሳ የሚወሰድባት የማዕቀብ እርምጃ ለኢንዱስትሪ እና ለቴክኖሎጂ ዘርፏ የሚያስፈልጋትን ቁሳቁስ እና አገልግሎት እንዳታገኝ ማድረግን እንደሚጨምር ተገልጿል።

ዋይት ሀውስ ባወጣው መግለጫ ዩክሬን በጀቷን ለመሸፈን እንድትችል የጂ ሰባት ቡድን በሚሰጣት እርዳታ ዩናይትድ ስቴትስ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር እንደምትለግስ አስታውቋል።

የቡድን ሰባት ሀገሮች ዩክሬንን የሚያስፈልጋትን የገንዘብ፣ የሰብዐዊ ረድዔት፣ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ በዘላቂነት እንደሚሰጧት ካሁን ቀደም ባልታየ ደረጃ ቃል በመግባት ላይ መሆናቸውን የዋይት ሀውሱ መግለጫ ጨምሮ አስረድቷል።

ጀርመን ውስጥ የተሰበሰቡት የቡድን ሰባት አባል ሀገሮች መሪዎች ድጋፉን ይፋ ባደረጉበት ጉባኤ ላይ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪን በኢንተርኔት አማካይነት አነጋግረዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ በሩሲያ ላይ የምትጥለው አዲስ ማዕቀብ የመንግሥቱን የመከላከያ ኩባኒያዎች እና የመከላከያ ምርመር ተቋማቷን የሚያካትት ሲሆን በጦርነቱ የወደሙባትን ቁሳቁሶች መተካት እንዳትችል የሚያደርግ እና የሩሲያ ወርቅ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገባ የሚከለክል መሆኑ ተገልጿል።

የቡድን ሰባት መሪዎቹ በተጨማሪም ሩሲያ በምትልከው ነዳጅ ላይ የዋጋ ገደብ ለመጣል እና በሌሎቹም ወደውጭ በምትልከው ሸቀጣ ሸቀጥ ላይ ከፍ ያለ ቀረጥ ለማስከፈል አቅደዋል። ዩክሬን ላይ የምታካሂደውን ጦርነት በሚደግፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ባለሥልጣናት እና ድርጅቶች ላይ አዳዲስ ማዕቀቦች እንደሚጥሉ ተመልክቷል።

የጦርነቱን ውሎ በሚመለከት የሩሲያ ወታደሮች ዛሬ ሰኞ የምስራቅ ዩክሬንን ሊቻንስክ ከተማ መደብደባቸው ተገልጿል። ሩሲያ ባሁኑ ወቅት የምስራቅ ዶንባስ አካል የሆነችውን ሉሃንስክ ክፍለ ግዛትን በሙሉ በሚያሰኝ ደረጃ ተቆጣጥራለች።

ትናንት ዕሁድ የሩሲያ ኃይሎች በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ እና ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ በሆነችው ኻርኺቭ ላይ የሚሳይል ጥቃት አድርሰዋል። የኪየቭ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ በሰጡት ቃል መዲናዋ ላይ በደረሰው ጥቃት ሁለት የመኖሪያ ህንጻዎች መመታታቸውን እና አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች አራት ሰዎች መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ ኪየቭ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት አስመልክተው "የተለመደውን አረመኔነቷን የሚያሳይ ነው" ብለዋል።

XS
SM
MD
LG