የደቡባዊ ዩክሬን ማሪዮፖል ከተማ ሩሲያ ሰብዓዊ እርዳታ ማስገቢያ መስመር ለመክፈት እና ነዋሪዎችን እንዲወጡ እፈቅዳለሁ ብላ የገባችውን ቃል ታከብር እንደሆን በመጠባበቅ ላይ ነች። የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ቃል አቀባይ ዛሬ ሲናገሩ
"እንደሚሆን ተስፋ አለን፣ ወደማሪዮፖል ለመንቀሳቀስ እየተዘጋጀን ነን፣ ነገር ግን ዛሬ ይሁን አይሁን አናውቅም" ብለዋል።
ትናንት የሩሲያ ኃይሎች እርዳታ የሚያጓጉዙ መኪናዎችን እና ነዋሪዎችን የሚያወጡ አውቶቡሶችን አስቁመዋል። ከፍተኛው የቱርክ ዲፕሎማት ሀገራቸው ሁለቱን ወገኖች ተመልሰው ወደድርድሩ ጠረጴዛ እንዲመለሱ ለማድረግ እየጣረች መሆኗን ገልጸዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ሁለት ከፍተኛ ጄኔራሎችን ማዕረጋቸውን መግፈፋቸው ተገለጠ:: "ለከሃዲዎች ጊዜ የለንም" ያሉት ፕሬዚዳንቱ ወደፊት ደግሞ ቅጣታቸውን ያገኛሉ ብለዋል።
በሌላ በኩል የዩክሬን ባለሥልጣናት እንዳሉት የሩሲያ ኃይሎች ከኪየቭ አካባቢ ሰባት መቶ የሚሆኑ ወታደራዊ መሳሪያዎችን አንስተው ወደቤላሩስ ወስደዋል።
አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣን በበኩላቸው የሩሲያ እንቅስቃሴ አነስተኛ እንደሆነ ገልጸው ሩሲያ ኃይሎች ኪየቭ እና ሌሎች ከተሞችን በአየር እና በመድፍ መደብደባቸውን እንደሚቀጥሉ አስጠንቅቀዋል።
በተያያዘ ዜና የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከተቀማጭ ነዳጅ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እንዲለቀቅ ትናንት ትዕዛዝ ሰጥተዋል። የሚለቀቀው ነዳጅ መጠን በመጠኑ ከምንጊዜውም ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።
ለስድስት ወራት በየቀኑ አንድ ሚሊዮን በርሜል እንዲለቀቅ ነው ፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ የሰጡት።