የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በብራስልስ በኔቶ አባላት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከተካፈሉና ዛሬ ዓርብ ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቫን ደር ሌይን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ወደ ፖላንድ አምርተዋል፡፡
ባይደን ከቫን ደር ሌይን ጋር በነበራቸው ቆይታ አውሮፓ በሩሲያ የተፈጠሮ ጋዝ ላይ ካላት ጥገኝነት በምትላቀቅበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
“የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከኃይል ምንጭ ሽያጭ የሚያገኙትን ትርፍ በዩክሬን ጦርነት በማዋል ይጠቀሙበታል” ያሉት ባይደን “የአሜሪካ ህዝብ ፑቲን በዩክሬን ህዝብ ላይ የሚያካሂዱትን አረመኔያዊና ኢፍትሃዊ ጦርነት በመደጎም የማይሳተፉ መሆኑን ግልጽ ማድረግ እንደማይፈልጉ” ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነር ቫን ደር ሌይን በበኩላቸው “የሩሲያን የጭካኔ ጦርነት ለማቆም ቁርጠኞች ነን” ያሉ ሲሆን “ ይህ ጦርነት የፑቲን ስትራቴጂካዊ ውድቀት ይሆናል” ብለዋል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ዓመት 15 ቢሊዮን ኪዩቢክ የተፈጥሮ ጋዝ ለአውሮፓ የምታቀርብ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ባይደን በፖላንድ ቆይታቸው በምስራቅ ክፍለ ግዛት ዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ወደ ሚገኘው ረዚስኮው እንደሚጓዙም ተነገሯል፡፡ ፖላንድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዩክሬን ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡
ባይደን ትናንት ሀሙስ ጧት በሰጡት መግለጫ ሩሲያ በዩክሬን የኬሚካል መሳሪያዎችን የምትጠቀም ከሆነ የም ዕራባውያን ጦርም አጸፋ እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡
በኔቶ ዋና ጽ/ቤት ንግግራቸውም ሩሲያ ከበለጸጉት የቡድን 20 አባል አገሮች ተሰርዛ ዩክሬን በቡድን 20ው ስብሰባ እንድትካፈል ሊፈቅድላት ይገባል ብለዋል፡፡
ባይደን በጦርነቱ ለተጎዱ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዩክሬናውያን ሰብአዊ እርዳታ ዩናይትድ ስቴትስ ከ1ቢሊዮን ዶላር በላይ መስጠቷን አስታውቀዋል፡፡